ቀጥታ፡

የበቀል በትሩን በንፁሀን ዜጎች ላይ ያሳረፈውን ህወሓት ለመደምሰስ በጋራ ልንነሳ ይገባል

ባህር ዳር፣  ጥቅምት 25/2014 (ኢዜአ) "በሰሜን ዕዝ ላይ ክህደት ከፈፀመ በኋላ የበቀል በትሩን በንፁሀን ዜጎች ላይ ያሳረፈውን ህወሓት ለመደምሰስ ኢትዮጵያዊያን በጋራ ልንነሳ ይገባል'' ሲሉ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ጥሪ አቀረቡ።

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ በአሸባሪው ህወሓት ጥቃት የተፈፀመበት አንደኛ ዓመት የዝክረ ሰማዕታት ቀን ዛሬ በባህርዳር ታስቦ ውሏል።   

አፈ ጉባኤዋ ፋንቱ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት አሸባሪው ህወሓት በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ክህደት ከፈፀመ በኋላ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሚሰሩ ኃይሎች ጋር ያለውን ህብረት በተግባር እያሳየ ነው።

ሀገር ለማፍረስ አጀንዳ አድርጎ የተነሳውን አሸባሪ የኢትዮጵያ ህዝብ ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ ከዳር እስከ ዳር "ሆ" ብሎ መነሳቱንና በአሁኑ ወቅትም ቃል ኪዳኑን እያደሰ መሆኑን ተናግረዋል።  

የጥፋት ቡድኑ ከ20 ዓመት በላይ በቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ሆኖ የትግራይን ህዝብ ሲጠብቅና ሲያገለግል በኖረው የሰሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ ታሪክ የማይሽረው ግፍ ፈጽሟል።

"ይህ አሸባሪ ቡድን በዕዙ ላይ የፈፀመውን አስነዋሪ ክህደት ዛሬም በንፁሀን ዜጎች ላይ አጠናክሮ በመቀጠል የበቀል በትሩን እያሳረፈ ይገኛል" ብለዋል።

የዝክረ ሰማዕታትን ቀን አስበን ስንውል የእነሱን ራዕይ መላው ህዝብና የመንግስት ሠራተኛ በተሻለ እንዲገነዘብ የተሻለ እድል ይፈጥራል።

ኢትዮጵያ አሁን ከተጋረጠባት ወቅታዊ የሕልውና አደጋ ለማዳን ሁሉም ዝግጁ እንዲሆን መልካም አጋጣሚ መፍጠሩንም ነው ።

ዕለቱ ልምድ ያላቸው ተዋጊዎች ክልሉ ያስተላለፈውን ጥሪ ተቀብለው ዝግጁነታቸውን ያረጋገጡበትና ቃል ኪዳናቸውን ዳግም ያደሱበት መሆኑንም አፈ ጉባኤዋ ገልፀዋል።

የክልሉ ህዝብ የተላለፈውን የክተት ጥሪ ተከትሎ እየሰጠ ያለውን ምላሽ አጠናክሮ በመቀጠል ይህንን አሸባሪ የህወሓት ቡድን ለመደምሰስ መዘጋጀት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

"በአንዳንድ አካባቢዎች የውስጥ ባንዳዎች ከአሸባሪው ህወሓት ጋር በጥቅም ተሳስረው የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ነቅተን መከታተልና አካባቢያችንን መጠበቅ ይገባናል" ሲሉም አሳስበዋል።

ማህበራዊ አንቂዎችም ሀገር ሊበትን ከሚችል ተግባር ተቆጥበው ኢትዮጵያን አንድ በሚያደርግ ጉዳይ ላይ አተኩረው እንዲሰሩ መክረዋል።

"እየታገልን ያለነው ኢትዮጵያንና ሕዝቧ ለማዳን ነው'' ያሉት አፈ ጉባኤዋ፣ መንግስት ያደረገውን ጥሪ መላው ህዝብ ተቀብሎ በሚችለው ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

አሸባሪው ሀወሓት አማራን ካፈረስኩ ኢትዮጵያን ማፍረስ እችላለሁ ብሎ መነሳቱን ጠቁመው፣ ህዝቡ ልዩነቱን ትቶ አንድነቱን በማጠናከር ኢትዮጵያን እንዲታደግ ጥሪ አቅርበዋል።

የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ አቶ ደረጀ መኮንን በበኩላቸው "አሸባሪው ህወሓት ህዝባዊ ማዕበልን ተጠቅሞ እንደወረረን ሁሉ እኛም በጋራ ተነስተን ልንመክተውና ልንደመስሰው ይገባል" ብለዋል።

"እነሱ ኢትዮጵያን ለመበተን ከውጭ ኃይል ጋር በአንድነት እንደቆሙ ሁሉ እኛም ጥቅምት 24ን ስናስብ የመንግስትን የክተት ጥሪ ተቀብለን የበኩላችንን ለመወጣት ቃል በመግባት መሆን አለበት" ሲሉም አክለዋል።    

"በአሸባሪው ህወሓት አሉባልታ ከመሸበር ወጥተን ሁላችንም ትግሉን በቁርጠኝነት በመቀላቀል ሀገራችንን ከብተና ልንታደግ ይገባል" ያሉት ደግሞ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ አቶ ሰሎሞን ንጋቱ ናቸው።

የሽብር ቡድኑ አምና በዛሬው ቀን በመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ የፈጸመው ዘግናኝ ግፍ የፈጠረውን ቁጭት መካስ የሚቻለው ሀገርን በማስቀደም ቡድኑን ማጥፋት ሲቻል መሆኑን ተናግረዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም