ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን የማዳን ተግባርን ከምንጊዜውም በላይ ተቀዳሚ አጀንዳ በማድረግ እንረባረባለን

ድሬዳዋ ፤ ጥቅምት 24/2014(ኢዜአ)''ኢትዮጵያን የማዳን ተግባርን ከምንጊዜውም በላይ ተቀዳሚ አጀንዳ በማድረግ እንረባረባለን''ሲሉ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ተናገሩ።

''አልረሳውም!እኔም የኢትዮጵያ ሠራዊት ነኝ!'' መሪ ሀሳብ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ አባላት የተፈጸመውን ጭፍጨፋ  በድሬዳዋ ዛሬ ደም በመለገስና ሌሎች   ሥነ-ሥርዓቶች ታስቧል።

ከንቲባ ከድር በወቅቱ እንደተናገሩት ፤ የሀገርን  ዳር ድንበር  ሲጠበቅ በነበረው ሠራዊት ላይ አሸባሪው ህወሃት የወሰደውን ጭካኔ የተሞላበት ጭፍጨፋ ሁሌም ሲታሰብ ይኖራል።

አስተዳደሩና ነዋሪዎቹ ይህን ሀገር አፍራሽ ቡድንና ተላላኪዎቹን በመደምሰስ የኢትዮጵያን የህልውና ማረጋገጥ ዘመቻ በስኬት እንዲጠናቀቅ ቀዳሚ አጀንዳ አድርገው ይሰራሉ ብለዋል።

ወጣቶች ከፀጥታ አካላት ጋር የአካባቢያቸውን ሰላምና ፀጥታ ከመጠበቅ ባሻገር ወደ ግንባር በመዝመት እያደረገ ያለውን ተሳትፎ እንዲያጠናክርም  ጥሪ አቅርበዋል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተሳተፉት ወይዘሮ አይነአዲስ አወቀ ፤ሀገርን የማዳን ተግባር የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን ይናገራሉ።

የአሸባሪውን ቡድን ከፋፋይ የውሸት ፕሮፓጋንዳ በተቀናጀ መንገድ ለማክሸፍ ከማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለሀገር ክብርና ልዕልና የተሰዉ  የመከላከያ ሠራዊት አባላትን ደም በመለገስ ማሰብ ብቻ ሳይሆን፤ ተልዕኮው በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ግንባር ለመዝመት መዘጋጀታቸውን የገለጸው ደግሞ ወጣት ፈልመታ መሐመድ ነው።

"ድልን በሰራዊቱ ትከሻ ላይ ብቻ ማስቀመጥ ሳይሆን ወጣቱ በህልውና ዘመቻ ላይ በተደራጀ መንገድ ከሠራዊቱ ጎን መሰለፍ አለበት" ብሏል።

ሌላዋ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ከድጃ አብዱልሸኩር፤ ሀገርን ለማዳን መተኪያ የሌለውን ሕይወቱን ለሚሰጠው ሠራዊት ደም መስጠት ኢምንት ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

"የአካባቢውን ሕዝብ በተለይም ሴቶችን በማደራጀት ለሠራዊቱ ስንቅ በማዘጋጀት ተልዕኮው እንዲፋጠን እሰራለሁ" ብለዋል።

ወይዘሪት ሕይወት ገብረአምላክ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች  በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን በተሰበረ ልብ መፀለይ አለባቸው  ብላለች።

ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ደም የለገሱት ወይዘሪት ሄለን ሽጉጤ ''ወጣቶች የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ ከመጠበቅ በሻገር የአሸባሪውን ተላላኪዎች አጋልጠን በመስጠት ለሀገሪቱ ህልውና የድርሻችንን ማበርከት አለብን'' ብላለች።

የሥነ- ሥርዓቱ ተሳታፊዎች ደም የተለገሰ ሲሆን፤ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ያላቸውን ክብርና ፍቅር አንጸባርቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም