በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ወታደራዊ ስልጠና የወሰዱ ዕጩ ዲፕሎማቶች ተመረቁ

245
አዲስ አበባ  ነሀሴ 13/2010  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሜጀር ጄነራል ሀየሎም አርአያ ወታደራዊ አካዳሚ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ወታደራዊ ስልጠና የወሰዱ ዲፕሎማቶችን  አስመረቀ፡፡ በወታደራዊ አካዳሚው ዛሬ በተካሄደ የምርቃት ሥነ- ስርዓት ስልጠናውን ላገኙ 89 ዕጩ ድፕሎማቶች የምስክር ወረቀት ተበረክቷል። ስልጠናውን ያገኙት 34 ሴቶችና 55 ደግሞ ወንዶች ናቸው። ከሐምሌ 15 እስከ ነሐሴ 13 ቀን 2010 ዓ ም ሆለታ በሚገኘው ሜጀር ጄነራል ሀየሎም አርአያ ወታደራዊ አካዳሚ ዲፕሎማቶቹ በንድፈ ሐሳብና በተግባር የተደገፈ ስልጠና አግኝተዋል። ሕገ-መንግሥት፣ አገራዊ እሴቶችና ስኬቶች፣ ወታደራዊ ባህልና ጨዋነት፣ ወታደራዊ ስነ-ልቦና፣ የጦርነት መሰረተ ሀሳቦች ላይ የንድፈ ሐሳብ ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል። የአካል ብቃት፣ የሰልፍ ልምምድ ጉዞዎች፣ የሰዓት አጠቃቀም፣ የጦር መሳሪያ ባህርያትና የተኩስ ልምምድ በተግባር ስልጠና ተካተው ተሰጥተዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት ''የነበረውን ከባድ ጫና ተቋቁማችሁ ለምረቃ በመብቃታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ'' ብለዋል። ''ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ የምትጫወተውን ሚና አስተማማኝ ለማድረግ የዕጩ ዲፕሎማቶች ሚና ትልቅ አቅም ይፈጥራል'' ያሉት ሚኒስትሩ አገሪቷ ኢጋድን ከመምራት ጀምሮ ያለባትን ኃላፊነት እየተወጣች መሆኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ የምትጫወተውን ሚና የበለጠ ለማጉላት ታታሪና ወጣት ዲፕሎማቶችን ማፍራት እንዲሚያስፈልግ ገልጸው በስነ-ምግባር የታነጹና አገር ወዳድ ዲፕሎማቶችን መፍጠር ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል። ተመራቂዎች በስልጠና ወቅት ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ አገራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። አገሪቱ በለውጥ ጎዳና ላይ እንደምትገኝ የተናገሩት ሚኒስትሩ ለውጡ የሁሉንም ጥረትና ጥንካሬ የሚጠይቅ በመሆኑ እጩ ዲፕሎማቶቹ በሙያቸው የአገሪቱን ሰላምና የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል። የአካዳሚው ዋና አዛዥ ብርጋድየር ጄነራል ክንፉ ገዙ በበኩላቸው ዲፕሎማቶቹ በአንድ ወር ቆይታቸው በንድፈ ሀሳብና በተግባር የታገዘ ስልጠና መውሰዳቸውን አበራርተዋል። ዋና አዛዡ አካዳሚው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር የሚኖረውን ትብብር የበለጠ በማጠናከር በቀጣይም አቅሙ በሚፈቅደው ሁሉ ተመሳሳይ ስልጠና እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል። ተመራቂዎች በበኩላቸው ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት በቆይታቸው ያገኙትን እውቀት ከሚሰሩት ስራ ጋር በማዋሀድ አገሪቷን በዲፕሎማሲው መስክ  ውጤታማ ለማድረግ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። በምርቃት ሥነ-ስርዓቱ ማጠቃለያ ላይም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የሜጀር ጄነራል ሀየሎም አርአያ ወታደራዊ አካዳሚ ሙዝየምን ጨምሮ የተለያዩ ቦታዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። ለስልጠናው መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላትም እውቅና ተሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም