መንግስት በትግራይ ክልል ወደ ህግ ማስከበር የገባው የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂ ኃይሎች የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በመፈጸማቸው ነው - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት በትግራይ ክልል ወደ ህግ ማስከበር የገባው የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂ ኃይሎች የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በመፈጸማቸው ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 24/2014 (ኢዜአ) መንግስት በትግራይ ክልል ወደ ህግ ማስከበር የገባው የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂ ኃይሎች የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በመፈጸማቸው መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ቢሮ በጋራ ያወጡት ሪፖርት አረጋገጠ።
አሸባሪው ህወሃት ‘ሳምሪ’ በሚል ያደራጃቸው ወጣቶች በማይካድራ ከ200 በላይ የአማራ ተወላጆችን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደላቸውንም ነው ሪፖርቱ ያረጋገጠው።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ቢሮ በትግራይ ክልል ተፈጸሙ የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በሚመለከት ሲያከናውን የቆየውን የምርመራ ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡
የጣምራ ቡድኑ ሪፖርት መንግስት በትግራይ ክልል ወደ ህግ ማስከበር የገባው የአሸባሪው ህወሃት ታጣቂ ኃይሎች የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በመፈጸማቸው መሆኑን ማረጋገጡን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ ተናግረዋል፡፡
ሪፖርቱ የኢትዮጵያ መንግስት “በትግራይ ክልል ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅሟል” በሚል ሲቀርብ የነበረውን ክስ በሚመለከት "ድርጊቱ መፈጸሙን የሚያሳይ ምንም አይነት ማረጋገጫ አላገኘሁም" ሲል አመላክቷል፡፡
በተጨማሪም በጥናቱ የዘር ማጥፋት ወንጀል መከሰቱን የሚያረጋግጥ ምንም ዓይነት ማስረጃ አለመገኘቱን ኮሚሽነሩ ዶክተር ዳንኤል ተናግረዋል፡፡
በተያያዘ የጣምራ ቡድኑ ሪፖርት አሸባሪው ህወሃት “ሳምሪ” ሲል ያደራጃቸው ቡድኖች በማይካድራ ከ200 በላይ የአማራ ተወላጆች ላይ ዘርን መሰረት ያደረገ ጥቃት ስለመፈጸማቸው ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡
ጣምራ ቡድኑ ጥናቱን ካለማንም ጣልቃ ገብነትና ጫና ማከናውኑን ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ የጉዳቱ ሰለባዎችን በማነጋገር ምርመራውን እንዳከናወነ ነው የገለጸው፡፡