ቀጥታ፡

ጀግኖችን ስናስብ የሽብር ቡድኑን ግብአተ መሬት በተባበረ ክንድ ለማጠናቀቅ ቃል በመግባት ነው

ጎንደር ፤ ጥቅምት 24/2014 (ኢዜአ) ጥቅምት 24ትን ስናስብ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሽብር ቡድኑን ግብአተ መሬት በተባበረ ክንድ ለማጠናቀቅ ቃል በመግባት ነው ሲሉ በሰሜን ጎንደር ዞን የደባርቅ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

''አልረሳውም እኔም የኢትዮጵያ ሠራዊት ነኝ'' በሚል መሪ ሃሳብ  ነዋሪዎቹ ዕለቱን በህሊና ጸሎት አስበውታል፡፡

ነዋሪዎቹ በወቅቱ እንዳሉት፤  የህወሓት ቡድን ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ክህደት ሀገረ አፍራሽነቱን ያጋለጠ እኩይ ተግባር ነው፡፡

ወይዘሮ የሻለም ሃይለማርያም በሰጡት አስተያየት፤ በደምና አጥንቱ የሀገሩን ዳር ድንበር እያስከበረ ያለው ሠራዊታችን ላይ በህወሓት የሽብር ቡድን የተፈጸመበት ክህደት ታሪክ ይቅር አይለውም ነው ያሉት፡፡

ዕለቱን የሚያስቡት የሽብር ቡድኑ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ክህደት መፈጸሙንና ሀገር የማፍረስ ዓላማው እንዳልተሳካ በዓለም አደባባይ እንዲጋለጥ ለማሳየት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

"ጥቅምት 24ትን ስናስብ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሽብር ቡድኑን ግብአተ መሬት በተባበረ ክንድ ለማጠናቀቅ ቃል በመግባት ነው'' ያሉት ደግሞ አቶ ጎሹ በላይነህ ናቸው፡፡

"ከህዝብ አብራክ የወጣው ሠራዊታችን ለ20 ዓመታት በትግራይ ምድር ሀገርና ህዝብ በመጠበቅ ህዝባዊ ወገንተኝነቱ ቢያረጋግጥም ምላሹ 'እህል ላበደረ ጠጠር' ሆኖበታል" ብለዋል፡፡

የአሸባሪው ድርጊት እሳቸውን ጨምሮ ሌላውንም ኢትዮጵያዊ በማስቆጣት ቁጭት መፍጠሩን ገልጸው፣ ህዝቡ ባሳየው የደጀንነት ተግባር ሠራዊቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለድል መብቃቱን አስታውሰዋል።

የህግ ማስከበር ዘመቻው በተጀመረ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ መከላከያ ሠራዊታችን ራሱን አጠናክሮ ትግራይን ከመቆጣጠር ባለፈ የተወሰኑ የቡድኑ አመራሮችን እስከመያዝ መድረሱንም ጠቅሰዋል።

የሽብር ቡድኑ በሰሜን እዝ ላይ የፈጸመው ጥቃት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያለውን ፍላጎት በአደባባይ ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።      

በጠንካራ ስነ-ልቦና የተገነባ ሠራዊት ምንጊዜም ለድል እንደሚበቃ ያመለከቱት አቶ ጎሹ፣ ዛሬም ህዝቡ ከሠራዊቱ ጎን መቆሙን በተግባር እያሳየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሻምበል ባሻ አሻግሬ ጌጡ  በበኩላቸው፣ "የሽብር ቡድኑ የህዝባችን አለኝታና መከታ በሆነው ሠራዊታችን ላይ የፈጸመው ክህደት ሀገር የማፍረስ ግቡን በይፋ ያወጀበት እለት ነው" ብለዋል፡፡

ቡድኑ የለኮሰው ጦርነት ሳይበቃ በደረሰባቸው የአማራ እና አፋር አካባቢዎች ንጹሀንን ከመጨፍጨፍ ባለፈ የግለሰብና የሀገር ሀብት እየዘረፈና እያወደመ መሆኑን አውስተዋል።

በሰራዊታችን ዳግም ጥንካሬ የሽብር ቡድኑ አከርካሪው ተመቶ ቢበታተንም ዳግም ለጥፋት ተልእኮ ተሰባስቦ በእኩይ ድርጊት ላይ መሰማራቱን ተናግረዋል።

"ዛሬ ጥቅምት 24ትን የምናስበው የቡድኑን ይህን አረመኔያዊ ተግባር ለመመከት ህዝባዊ አንድነታችን ለማጠናከር ቃል በመግባት ነው" ብለዋል።

ዕለቱ የጥፋት ቡድኑ በደባርቅና በዳባት ግንባር የደረሰበትን የሽንፈት ጽዋ በሌሎች የአማራ ክልሎች ለመድገም የሚነሳሱበት ጭምር  መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የደባርቅ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክተል ከንቲባ አቶ ብርሀኑ ፀጋዬ ፤ ህወሓት በሀገርና በህዝብ ላይ የፈጸመው ክህደት ኢትዮጵያዊያንን ከማስቆጣት ባለፈ አንድ ሆነው ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል ቁጭት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።

''ዛሬም ይህን የውጭ ሀይል ተላላኪ ባንዳ ነቅለን ለመጣል በእልህ፣ በወኔና በህብረት ከተንቀሳቀስን ድላችንን የምናበስርበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም'' ብለዋል፡፡

በመታሰቢያ ሥነ-ሥርዓቱ  የከተማውና አካባቢው ነዋሪዎች፣ የመከላከያ፣ የልዩ ሃይልና የሚሊሻ አባላት እንዲሁም የከተማ አስተዳደር አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም