ቀጥታ፡

የአሸባሪው ህወሃት ደጋፊ ሚዲያዎች የ "በሬ ወለደ" ክስ እና የጥምር ቡድኑ ጥናት ሪፖርት!

የአሸባሪው ህወሃት ደጋፊ ሚዲያዎችና ተቋማት የኢትዮጵያ መንግስት “በትግራይ ክልል የዘር ማጥፋትን ፈጽሟል፤ ረሃብን የጦር መሳሪያ እየተጠቀመ ነው” ሲሉ ሲያቀርቡት የቆዩት ክስ ምንም አይነት ማረጋገጫ እንዳልተገኘበት የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት አመላክቷል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽን ቢሮና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በትግራይ ክልል ተፈጸሙ የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በሚመለከት ሲያከናውን የቆየውን ጥናት ሪፓርት ይፋ አድርጓል፡፡

አሸባሪው ህወሃት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በመከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ አባላት ላይ አሰቃቂ ጥቃት በመፈጸም የፌደራል መንግስት ተገዶ ወደ ጦርነት አንዲገባ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

የአሸባሪው ህዋሃት አፈ-ቀላጤዎች በወቅቱ የሰሜን እዝ አባላትን ለመቆጣጠር ሲባል "በ45 ደቂቃ ውስጥ እዙ ላይ መብረቃዊ ጥቃት" መፈጸሙን ቢገልጽም የዓለም አቀፍ ተቋማትና መገናኛ ብዙሃን ግጭቱ “እንዴት ተጀመረ” የሚለውን ጉዳይ ብዙም ትኩረት ሲሰጡት አይስተዋልም፡፡

ዛሬ የወጣው የጥምር ቡድኑ ሪፖርት ግን ግጭቱን የህወሃት አሸባሪ ቡድን በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በመፈጸም የእዙን ማዕከልና መሳሪያ ተቆጣጥሯል” ሲል ግጭቱን ማን እንደጀመረው ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡

ነገር ግን ባለፈው አንድ ዓመት አንዳንድ የዓለም አቀፉ መገናኛ ብዙሃንና ተቋማት በትግራይ ክልል በተከሰቱት ሁሉም ጉዳዮች የኢትዮጵያ መንግስትን ተጠያቂ የሚያደርጉ ጭፍን ዘገባዎችን ሲያሰራጩ ቆይተዋል፡፡

የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በተደራጀ መልኩ በተለይ “የኢትዮጵያ መንግስት ርሃብን እንደ ጦር መሳሪያ በመጠቀም የዘር ማጠፋት እየፈጸመ እንደሆነ” አስመስለው  የተዛባ መረጃ በማሰራጨት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲፈጥር ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡

አንዳንድ የዓለም አቀፍ ተቋማት ደግሞ ያለምንም ጥናት የመገናኛ ብዙሃንን ድምጽ ተከትለው የኢትዮጵያ መንግስት ሆነ ብሎ የትግራይ ህዝብ ለርሀብ እንዲጋለጥ ማድረጉን በግልጽ ሲከሱ ቆይተዋል፤ እየከሰሱም ይገኛሉ፡፡

ለአብነትም ታዋቂው የዜና የውታር ‘አሶሴትድ ፕሬስ ’በሰኔ 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ርሃብን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅሟል ሲል ዘገባ መስራቱ ይታወሳል፡፡

ይህን ተከትሎም ሮይተርስና ዋሽንግተን ፖስት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ከፍተኛ ኃላፊ ከሆኑ ግለሰቦች መካከል ማርክ ሎኮክ የኢትዮጵያ መንግስት ርሃብን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀመ መሆኑን መግለጻቸውን አስነብበዋል፡፡

በተጨማሪ የእንግሊዙ ግዙፍ የመገናኛ ብዙሃን ተቋም “ቢቢሲ” እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ሰኔ 2021 ተመሳሳይ ዘገባን አስራጭቷል፡፡

እነዚህ ዘገባዎችን ተከትሎም አንዳንድ የዓለም አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ውርጅብኝና ጫና ሲፈጽሙ ቆይተዋል፡፡

በዚህ ሁሉ ሂደት ግን  የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል የሚኖሩ ዜጎች ለችግር እንዳይጋለጡ የሰብዓዊ ድጋፍ በአየርና የብስ እንዲጓጓዝ አበክሮ ሲሰራ ቆይቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ሰኔ 22 ቀን 2013 ዓ.ም  እንደገለጹት፤ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የትግራይ ክልልን ለቆ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ  የኢትዮጵያ መንግስት የትግራይ ክልልን መልሶ ለማቋቋምና የክልሉን ነዋሪዎች ለመደገፍ 100 ቢሊዮን ብር ወጪ አድርጓል፡፡

አሸባሪው ህወሃት የጥገና ባለሙያዎችን እየገደለ ጭምር መንግስት የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ወደ ስራ ለማስገባት  ከፍተኛ ርቀትን ተጉዟል፡፡

“አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም” እንዲሉ በዚህ ሁሉ ሂደት የዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ህወሃትን ቅዱስ በማድረግ “የኢትዮጵያ መንግስት ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀመ ነው” የሚል ክስ ብቻ ሲያስተጋቡ ቆይተዋል፡፡

አሸባሪው ህወሃት ሰብዓዊ ደጋፍ ወደ ትግራይ እዳይደርስ ማደናቀፍና ሰብዓዊ ድጋፍ ጭነው ወደ ትግራይ ክልል የሚገቡ ተሽከርካሪዎችን በማገት የአማራና አፋር ክልሎችን የሚወሩ ታጣቂዎችን ለማጓጓዝ እየተጠቀመባቸው እንኳ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለጉዳዩ ብዙም ጆሮ ሳይሰጠው ቆይቷል፡፡

ዛሬ የወጣው የጥምር ቡድኑ ሪፖርት ግን አጥጋቢም ባይሆን ጉዳዩ  እውን ስለመሆኑ አመላክቷል፡፡

የጥምር ቡድኑ ሪፓርት “የህወሃት ታጣቂ ኃይሎች መንገዶችን በመዝጋት የሰብዓዊና አስቸኳይ ጊዜ ድጋፎች በቶሎ እንዳይደርስ ሲያደርጉ ቆይተዋል” ሲል አሸባሪው ነዋሪዎች እንዲራቡ ሲሰራ መቆየቱን አረጋግጧል፡፡

ሪፖርቱ የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ እብንዳይደረስ በማዽረግ ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅሟል በሚለው ክስ ላይም ምላሽ ሰጥቷል፡፡

የጥምር ቡድኑ ሪፓርት የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ሆነ ብሎ የሰብዓዊ ድጋፍ ለህዝብ እንዳይደርስ በማስተጓጎል ርሃብን እንደ ጦር መሳሪያ እንደተጠቀመ በማስመሰል ሲቀርቡበት በነበረው  ክስ ላይ “ምንም አይነት አሳማኝ ማረጋገጫ አላገኘሁም”  ሲል ይፋ አድርጓል፡፡

በተጨማሪ የጥምር ቡድኑ የጥናት ሪፖርት በኢትዮጵያ “የዘር ማጥፋት መንጀል” ስለመፈጸሙ የሚያሳይ ማረጋገጫ አለማግኘቱን ይፋ አድርጓል፡፡

በዛሬው እለት በስዊዘርላንድ ጀኔቫ መግለጫ የሰጡት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሼል ባሽሌት በኢትዮጰያ የዘር ማጥፋት ወንጀል ስለመካሄዱ ማረጋገጫ አለመኖሩን ግልጸዋል፡፡

በተያያዘ የጥምር ቡድኑ የጥናት ሪፖርት አሸባሪው ህወሃት “ሳምሪ” ሲል ያደራጃቸው ነፍሰ በላ ቡድኖች በማይካድራ ከ200 በላይ የአማራ ተወላጆች ላይ ዘርን መሰረት ያደረገ ጥቃት ስለመፈጸማቸው ማረጋገጫ ሰጥቷል.፡፡

ከዚህ ቀደም የአሸባሪው ህወሃት ቡድን ቁንጮ አመራሮች በማይካድራ ዘርን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ እንዳልተደረገ በመካድ፤ ድርጊቱ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ጥሪ ሲያቀርቡ እንደነበር ይታወሳል፡፡

የጥምር ቡድኑ የጥናት ውጤት ድርጊቱ “ሳምሪ” በተሰኘ የአሸባሪ ቡድኑ ክንፍ መፈጸሙን አረጋግጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም