ከሃዲውን የህወሓት ቡድን ለመፋለም ተዘጋጅተናል- የሐረሪ ክልል ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ከሃዲውን የህወሓት ቡድን ለመፋለም ተዘጋጅተናል- የሐረሪ ክልል ነዋሪዎች
ሐረር፣ ጥቅምት 24 ቀን 2014(ኢዜአ) ከሃዲውንና ጨፍጫፊውን የህወሓት ቡድንን እስከ ግንባር ድረስ ዘምተው ለመፋለም መዘጋጀታቸውን የሐረሪ ክልል ነዋሪዎች ገለጹ።
በአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ግፍ አንደኛ ዓመት መታሰቢያ ''አልረሳውም እኔም የኢትዮጵያ ሠራዊት ነኝ!''ዛሬ መርሐ ግብር በሐረር ከተማ ተካሂዷል።
የመርሐ ግብሩ ተሳታፊዎች ለአገር መከላከያ ሠራዊት ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት ደም ለግሰዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው ተሳታፊዎች እንደተናገሩት ከሃዲው የህወሃት ቡድን ባለፈው አመት በሠራዊቱ ላይ የፈጸመው ግፍ የፈጠረባቸው ቁጭት የአገር አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስከበር የበለጠ አነሳስቷቸዋል።
ከተሳታፊዎቹ መካከል አቶ ግርማ በርሄ "የህወሀት ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓም በሰሜን ዕዝ ላይ የሰራው ግፍ መቼም የማልረሳውና ሁሌም የሚያንገበግበኝ ነው " ብለዋል።
"በውጭ ሃይሎች እየተጋለበ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚራወጠውን ቡድን በጽናት ለመፋለም ዝግጁ ነኝ " ሲሉ በአጽኖት ተናግረዋል።
አቶ አያልቅበት ቸርነት በበኩላቸው አሸባሪውና ወራሪው ህወሀት በመከላከያ ሰራዊትና በንጹሀን ላይ የፈጸመው ኢሰብዓዊ ድርጊት የሀገር ክህደትን በግልጽ ያሳየ መሆኑን አመልክተዋል።
''እንደ አባቶቻችን እኔም መስዋዕት በመሆን ሀገሬን ለማቅናት ተዘጋጅቻለሁ'' ብለዋል ።
አቶ አያልቅበት አባትና አያቶቻችን በጦርና በጎራዴ ያስጠበቋት ሀገር ስትፈራርስ ላለማየት ''እዘምታለሁ!'' ሲሉ ቁርጠኝነታቸውን ገልጸዋል።
አቶ ዱላ ማኖጂ በበኩላቸው "የጥፋት ሃይሉ ሰሜን ዕዝ አባላት ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋ ሳይበቃው እስከ ዛሬም ወጣቶችን እየገደለ፣ሴቶችን እየደፈረ፣ቅርሶችን እያወደመና የሃይማኖት ተቋማትን እያቃጠለ አሸባሪነቱን እያሳየ ነው " ብለዋል።
አሸባሪ ቡድኑን በተባበረ ክንድና በአንድነት ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመሰለፍ ለማጥፋት መነሳታቸውን አስታውቀዋል።
''ከክህደቶች ሁሉ የከፋ ክህደት የተፈጸመበት ዕለትና ሁሌም ከውስጤ የማይወጣ ነው፤ዕድሜ ልኬንም አልረሳውም፤ያንገበግበኛልም'' በማለት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓም በሰሜን እዝ አባላት ላይ የደረሰውን ጥቃት ያስታወሱት ደግሞ አቶ ፍሥሐ ሥዩም ናቸው።
አሸባሪው ቡድን ያሳደረብኝን ቁጭት ለመወጣት ስለምፈልግ በተጠየቅኩ ጊዜ ለመዝመት ዝግጁ ነኝ ብለዋል።
በክልሉ ምክር ቤት ቅጥር ግቢ በተከናወነው መርሐ ግብር ላይ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።