ቀጥታ፡

በሰሜን እዝ ባልደረቦቻችን ላይ የተፈፀመውን ጭፍጨፋ ስናስብ የአሸባሪውን ህወሃት ግብዓተ መሬት ለመፈጸም ቃል በመግባት ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 24/2014 (ኢዜአ) በሰሜን እዝ ባልደረቦቻችን ላይ የተፈፀመውን ጭፍጨፋ ስናስብ የአሸባሪውን ህወሃት ግብዓተ መሬት ለመፈጸም ቃል በመግባት መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የመከላከያ ሰራዊት አባላት ተናገሩ።

የህወሃት አሸባሪ ቡድን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ በሰሜን እዝ የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በማድርስ የአገር ክህደት መፈፀሙ ይታወሳል።

የአሸባሪው ድርጊት በተለይም ለትግራይ ህዝብ ልማት በሚያከናውን፣ የተቸገሩትን በሚያግዝ፣ የአቅመ ደካሞችን አዝመራ በሚሰበስብ የሰሜን እዝ ሰራዊት ላይ ነበር።

አሸባሪው ቡድን በሰሜን እዝ የሰራዊት አባላት ላይ ጥቃት የፈፀመበትን 1ኛ ዓመት በማስመልከት በመከላከያ ሚኒስቴር ቅጥር ግቢ ታስቧል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ ከተገኙት መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው የሰራዊት አባላት በሰሜን እዝ ባልደረቦቻችን ላይ የተፈፀመውን ጭፍጨፋ ስናስብ የአሸባሪውን ህወሃት ግብዓተ መሬት ለመፈጸም ቃል በመግባት ነው ብለዋል።

ከምንም በፊት አገርና ህዝባቸውን ለማስቀደም በቆራጥነት ሰራዊቱን መቀላቀላቸውን ገልጸው በካሃዲ የተደፈረችውን አገራችንን ክብሯን ለማስጠበቅ ተዘጋጅተናል ብለዋል።

ኢትዮጵያን ለማፍረስ የመጣውን የህወሃት ወራሪ ቡድን እስከወዲያኛው ለመደምሰስም በሙሉ ቁመና ላይ እንገኛለን ሲሉም አረጋግጠዋል።

ከኢትዮጵያ ህዝብና ሰራዊት አቅም በላይ የሚሆን አሸባሪ ሃይል አይኖረም ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ትናንትና ሲያደርግ እንደነበረው ሁሉ ዛሬም በታላቅ ጀግንነት ለሰራዊቱ ደጀን እንዲሆን ጠይቀው ወጣቶችም ሰራዊቱን በመቀላቀልና አገራቸውን በመጠበቅ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

"በአንድነት ከቆምን የኢትዮጵያን ጠላቶች ከማስወገድ የሚያግደን ሃይል የለም፤ አሸባሪውንም እናስወግደዋለን" ብለዋል።   

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል በሰራዊቱ ላይ በህወሃት አሸባሪ ቡድን የተፈፀመበት ጭፍጨፋ አንደኛ ዓመት በዛሬው እለት ታስቦ ውሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም