የጋምቤላ ክልል ሕዝብ ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ አሸባሪውን ህወሃትና ግብረ አበሮቹን እንዲደመስስ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የጋምቤላ ክልል ሕዝብ ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ አሸባሪውን ህወሃትና ግብረ አበሮቹን እንዲደመስስ ተጠየቀ
ጋምቤላ፣ ጥቅምት 24/2014(ኢዜአ) የጋምቤላ ክልል ሕዝብ ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ አሸባሪውን ህወሃትና ግብረ አበሮቹን እንዲደመሰስ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ዑጁሉ አስገነዘቡ።
’’አልረሳውም እኔም የኢትዮጵያ ሰራዊት ነኝ!’’ በሚል መሪ ሐሳብ በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው የግፍ ጭፍጨፋ አንደኛ ዓመት መታሰቢያ በጋምቤላ ክልል ታስቧል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በመታሰቢያ መርሐ ግብሩ ላይ እንዳሳሰቡት የክልሉ ሕዝብ የሽብርተኛ ቡድንና ተላላኪዎቹን ግብዓተ መሬት ለመፈጸም አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀት አለበት።
ቡድኑ ኢትዮጵያን በገዛበት 27 ዓመታት ያቀደውን አገር የመበታተን እኩይ ሴራ የትግራይን ሕዝብ ለጦርነት እየማገደ ለማስፈጸም ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል።
በመሆኑም የጥፋት ኃይሉን እኩይ ሴራ ለማምከን ለተጀመረው የሕልውና ዘመቻ ስኬት መላው የክልሉ ህዝብ በግንባር ከመሰለፍ እስከ ደጀንነት እንዲሰለፍ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።
ቡድኑ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ለሁለት አሥርት ዓመታት ሲጠብቀውና በችግርም ጊዜ አብሮት በነበረው የሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው ጭካኔ የተሞላበት ተግባር ምንጊዜም በኢትዮጵያ ህዝቦች ሲታሰብ ይኖራል ብለዋል።
አሸባሪው ቡድን በወቅቱ የፈጸመው ድርጊት ሰው በሆነ ፍጡር ፍጹም የማይታሰብ አረመኔያዊ ድርጊት መሆኑንም አቶ ዑሞድ ገልጸዋል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ ከታደሙት ነዋሪዎች መካከል አቶ አንዱአለም ብርሃኑ በሰጡት አስተያየት የአገርን ሕልውና ለማስጠበቅ ለተጀመረው ዘመቻ መሰዋትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ የታደሙት አሸባሪው ህወሓት በሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝን ላይ በፈጸመው ያልታሰበ ጥቃት የተሰው ጀግኖቻችንን ለማስታወስ እንደሆነም ተናግረዋል።
ወይዘሮ አባንግ ኦኬሎ በበኩላቸው የአሸባሪው ህወሓት ግብዓተ መሬት ለመፈጸም ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጎን እንደሚሰለፉ ገልጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የህወሓትና የሸኔ ተላላኪዎች ወደ ክልሉ ገብተው ችግር እንዳይፈጥሩም አካባቢያቸውን ነቅተው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
ሌለው ታዳሚ አቶ ታይዶር ቻምባንግ የአሸባሪውን ህወሓት አገር የማፍረስ ሴራ ለማክሸፍ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ልንነሳ ይገባል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በመርሐ ግብሩ በሰሜን ዕዝ የተሰው ጀግኖችን ለማስታወስ የፊርማ የማኖር ሥነ ሥርዓት ተካሄዷል።