ኢትዮጵያዊያን የአገራችን መከታ ሆነን በጋራ የምንቆምበት ጊዜው አሁን ነው

64

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24/2014(ኢዜአ) በአገር ህልውና ላይ የተደቀነውን አደጋ ለማክሸፍ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተፈጻሚ እንዲሆን ኢትዮጵያዊያን የአገራችን መከታ ሆነን በጋራ የምንቆምበት ጊዜው አሁን ነው ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአገር ህልውና እና ሉዓላዊነት ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመከላከል በመላው ኢትዮጵያ ለስድስት ወራት ተፈፃሚ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል።

አዋጁ ሽብርተኛው ህወሓትና የሽብር ግብረአበሮቹ በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች በንፁሃን ዜጎች ላይ እየፈፀሙ ያሉት ግድያ፣ ዝርፊያና ሌሎችም ከፍተኛ ጭካኔ የተሞላባቸው ኢ-ሠብዓዊ ጥቃቶች አደገኛ ደረጃ ላይ በመድረሳቸው አደጋውን ለመቀልበስ ነው የታወጀው።

ኢዜአ ይህንኑ አስመልክቶ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ትክክለኛ ውሳኔ ነው፤ ኢትዮጵያን ለመታደግ ሁሉም ዜጋ ወታደር መሆን ያለበት ጊዜው አሁን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ወጣት አሸናፊ ወልዴ አዋጁ ኅብረተሰቡ አረጋዊ፣ ሴት ወንድ ሳይል ከመንግስት ጎን ሆኖ አገሩን መጠበቅ እንዲችልና ግንባር ባይሄድ እንኳን አካባቢውን መጠበቅ እንዲችል ጠቀሜታ እንዳለው ገልጿል።

ሰርጎ ገቦችን በመለየትና አካባቢውን በመጠበቅ የተለየ እንቅስቃሴ ሲኖርም በመከታተልና በመጠቆም በአጭር ጊዜ ሠላም እንዲሰፍን መስራት ይኖርብናል ብሏል።

አቶ ስጋቱ ከድር በበኩላቸው አዋጁ ጊዜውን የጠበቀና ሁሉም የሚደግፈው ነው፤ ዜጎች አካባቢያቸውን በመጠበቅ የተረጋጋ ሠላም ለማስፈንም ይረዳል ብለዋል።

መንግስት ጦርነቱ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ ባወጣው አዋጅ መሰረት ሁሉም ዜጋ ወታደር ሆኖ አካባቢውን በመጠበቅ አዋጁ ተፈጻሚ እንዲሆን መተባበር አለበት ያለው ደግሞ ወጣት ግርማ አንድነው ነው።

አቶ ገላው ተሰማም አዋጁ ኅብረተሰቡ አካባቢውን እንዲጠብቅ የሚያደርግ በመሆኑ ተደራጅተን ልንጠብቅ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም