ቀጥታ፡

ከ16 ሺህ ቶን በላይ የምግብና ሸቀጣ ሸቀጥ ምርቶች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ተደርጓል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24/2014(ኢዜአ)የጥራት ደረጃቸውን ያልጠበቁ ከ16 ሺህ ቶን በላይ የምግብና ሸቀጣ ሸቀጥ ምርቶች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ማድረጉን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ገለጸ።

የባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አበራ ደነቀ፤ የበጀት አመቱን ሶሰት ወራት አፈፃፀም አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።  

በመግለጫቸውም በበጀት ዓመቱ ሶስት ወራት የጥራት ደረጃቸውን  ያልጠበቁ 16 ሺህ 697 ቶን የተለያዩ የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦችን  ከውጭ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ማገዱን ገልጸዋል።

ከታገዱት ምግቦች መካከል ስኳር፡ ሩዝ፡ የተለያዩ  የፍራፍሬ ጭማቂዎች (ጁሶች) እና የለስላሳ መጠጦች እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።

በሀገር ውስጥ ተመርተው ለገበያ በሚቀርቡ የተለያዩ ምርቶች ላይ ባደረገው ድንገተኛ ቁጥጥር ከባዕድ ነገር ጋር የተቀላቀሉ ከ4 ሺህ 300 ኪሎ ግራም በላይ ቅቤ እና 65 ኩንታል በርበሬ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ  6 ሚሊዮን 188 ሺህ 970 ቶን የተለያዩ የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦችን የጥራትና ደህንነት ቁጥጥር በማድረግ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ፍቃድ መስጠቱንም ጠቁመዋል፡፡

በተደረገው ቁጥጥር ከ220 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው ከውጭ ሊገቡ የነበሩ መድሃኒቶች መስፈርቱን ያላሟሉ ሆነው በመገኘታቸው ተመላሽ  ሆነዋል።

ከ7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው የህክምና መሳሪዎች የጥራት ቁጥጥር ተደርጎ ፈቃድ ሲሰጥ ከ2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ደግሞ የጥራት ደረጃቸው ዝቅተኛ ሆኖ በመገኘቱ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ተደርጓል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ባልተገባ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የተገኙ 20 የመድሃኒትና ህክምና መሳሪያዎች ጅምላ አከፋፋዮች ላይ ፈቃድ የመሰረዝ እና ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ በ8 የምግብ አምራቾች ላይ ጊዚያዊ እገዳ ተደርጓል ነው ያሉት።

ህብረተሰቡ የጥራት ደረጃቸውን ያልጠበቁ፣የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው እንዲሁም በህገ-ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የምግብና የመድሃኒት ምርቶችን በመጠቆም ለሚመለከተው አካል እንዲያሳውቅ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ቁጥጥሩን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የሕዝብ ግኑኙነት ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም