ቀጥታ፡

ሪፖርቱ አንዳንድ አገራት በተሳሳተ መረጃ ላይ ተመስርተው የወሰዱትን የፖሊሲ ርምጃ መልሰው እንዲያጤኑ ያግዛል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮ በጋራ ያወጡት ሪፖርት አንዳንድ አገራት በተሳሳተ መረጃ ላይ ተመስርተው የወሰዱትን የፖሊሲ ርምጃ መልሰው እንዲያጤኑ የሚያግዝ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገለጹ።

የሁለቱ ተቋማት አመራሮችና አባላት በጣም አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ፕሮፌሽናልና ተአማኒነት ያለው የሰብዓዊ መብት ምርመራ ለማድረግ ያደረጉትን ጥረትም አድንቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፣ በማህበራዊ ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት እንዳመለከቱት በቡድኑ ሪፖርት ላይ መንግስት የተወሰኑ ልዩነቶች ቢኖሩትም በቀጣይ ለሚወሰድ ርምጃ የሚያግዝና በመንግስት ላይ ያልተገባና መሰረተ ቢስ ውንጀላዎችን ሲሰነዝሩ ለነበሩ ወገኖች ምላሽ እንደሚሰጥ በፅሁፋቸው ጠቁመዋል።

ዛሬ ይፋ በተደረገው የቡድኑ ሪፖርት፣ የጦርነቱን አጀማመር መንግስት በግልፅ ሲያቀርባቸው በነበሩ ማስረጃዎች ላይ ጥርጣሬ ሲያነሱ ለነበሩ አንዳንድ ወገኖች  ምላሽ ሰጥቷል።

የሕወሓት የሽብር ቡድን በሰሜን ዕዝ ላይ በፈጸመው ጥቃት መነሻነት የአገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ ተቋማት ወደ እርምጃ እንዲገቡ ማድረጉን አመልክቷል።

ሪፖርቱ የመለሰው ሌላው ጉዳይ የሰብዓዊ ድጋፍ ክልከላና ረሀብን እንደ ጦር መሳሪያ የመጠቀም ተግባር ተፈፅሟል በሚል በአንዳንድ የውጭ መንግስታትና ተቋማት ሲቀርብ የነበረውን ክስና ውንጀላ መሰረተቢስነት ማጋለጡ ነው።

በቡድኑ ሪፖርት መሰረት በትግራይ ክልል ሆን ተብሎ የሰብአዊ እርዳታ እንዳይደርስ አልተደረገም፤ ረሃብም ለጦር መሳሪያነት ስለመዋሉ የሚያሳይ መረጃ አልተገኘም።

ይህም ውንጀላው መሰረተ ቢስና ፖለቲካዊ ፍላጎት ያዘለ ነው በሚል መንግስት በተደጋጋሚ ሲገለፅ የነበረውን እውነታ አረጋግጧል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ "የእኛ ጠላቶች" የዓለም አቀፍ ማህበረሰቡን ለማሳሳት ሳይታክቱ ሰርተዋል፤ ሁሌም እናውቅ የነበረው ክሶቹ ሀሰት መሆናቸውን ነበር"  ሲሉም አክለዋል።

የተፈበረኩት የሀሰት ክሶች እንደ እውነት መታየታቸውንና በዓለም ላይ በሚገኙ መገናኛ ብዙሃን በተደጋጋሚ ጊዜ ሲዘገቡ መቆየታቸውንም አውስተዋል።

በእነዚሁ ሀሰተኛ የዜና ዘገባዎች ላይ በመንተራስ አንዳንድ አገራት በኢትዮጵያ ላይ የወሰዷቸው የውጪ ፖሊሲ እርምጃዎችን ዳግም እንዲያጤኑ ሪፖርቱ እድል እንደሚፈጥርላቸውም እምነት እንዳላቸው አመልክተዋል።

ሀሰተኛ ዘገባዎቹን መነሻ ያደረጉ የፖሊሲ እይታዎቻቸው ኢትዮዽያ ከአገራቱ ጋር ያላትን የረጅም ጊዜ ግንኙነት መሸርሸሩንም ጠቁመዋል።

ሕወሓት የፈጸማቸው አሰቃቂ ድርጊቶችና ጥሰቶችን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ "ጆሮ ዳባ ልበስ" ብሎታል፤ ድርጊቱን አሳንሶ አይቶታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፣ የጋራ ምርምራ ቡድኑ ግኝቶች በብዙ መልኩ ከመንግስት ምርምራ ጋር ወጥነትና ተመሳሳይነት ያላቸው ናቸው ብለዋል።

ሕወሓት ግጭቱ እንዲጀመር ማድረጉን ሪፖርቱ በግልፅ ማመላከቱን በአብነት በማንሳት።

ሪፖርቱ አሸባሪው ህወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከሰነዘረበት ጊዜ አንስቶ እስከ ሰኔ 2013 ዓ.ም ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ጉዳይ ብቻ የተመለከተ በመሆኑ፣ መንግስት የተናጥል ተኩስ አቁም አድርጎ ከትግራይ ክልል ከወጣ በኋላ ሕወሓት ግጭቱን ወደ አፋርና አማራ ክልሎች በማስፋት የተለያዩ አሰቃቂ ድርጊቶችን እየፈፀመ መሆኑንም አመልክተዋል።

በዚሁ የሽብር ቡድን እየተፈጸሙ ያሉ የጭካኔ ድርጊቶች የከፋ ቀውስ እንዳያስከትሉ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ እንደሆነም ተናግረዋል።

በሪፖርቱ እንደተመለከተው በአንዳንድ ወታደሮችና የክልል የጸጥታ ሃይሎች "ፍርሃትና ጭንቀት የሚፈጥሩ" ጥሰቶችና ጥፋቶች መፈጸማቸውን የሚያሳየውን መረጃ መንግስት እንደሚቀበለውና ተፈጸሙ የተባሉትን ድርጊቶች በልዩ ትኩረት በማየት ድርጊቱን የፈጸሙ አካላትን መንግስት ወደ ፍትሕ የማቅረብ ስራ እያከናወነ ይገኛልም ብለዋል።

ለዚህም የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ያቀፈ ግብረ ሃይል ማቋቋማቸውን አመልክተዋል።

መንግስት የተፈጸሙ ድርጊቶችን በመመርመር እርምጃ ለመውሰድ ቁርጠኛ መሆኑንና የዜጎች ሰብአዊ መብት እንዲጠበቅ እንዲሁም የሕግ የበላይነት እንዲከበርና ግልጽ በሆነ የፍትሕ ስርዓት ተጠያቂነትን ለማስፈን እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ መንግስት ለጋራ ምርመራ ቡድኑ "በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የቀረቡ ተንኮል አዘልና መሰረተ ቢስ ክሶችን" አስመልክቶ ቅሬታዎች ቢያቀርብም ቡድኑ በጥናቱ እንዳላካተተው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስረድተዋል።

በወጣው ሪፖርት አንዳንድ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬዎች ቢኖሩንም በመንግስት በኩል ተጎጂዎች ተገቢውን ፍትህ እንዲያገኙ፣ ተጠያቂነት ለማረጋገጥና የመከላከል እርምጃዎችን ለመውሰድ ሪፖርቱ ጠቃሚ ሰነድ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም