ቀጥታ፡

አሸባሪውን ህወሃት በየትኛውም አውደ ግንባር መክቶ ለማሸነፍ መዘጋጀት አለብን

ጥቅምት 24/2014 አሸባሪውን ህወሃት ከጠመንጃ አፈ ሙዝ በተጨማሪ በኢኮኖሚ አሻጥርና ሌሎች የጥፋት መንገዶች የከፈተውን የውጊያ አውደ ግንባር በጋራ በመመከት ለማሸነፍ መዘጋጀት አለብን ሲሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ ገለጹ።

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አመራርና ሰራተኞች አሸባሪው ህወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመውን ጥቃት አንደኛ ዓመት በማስመልከት የመታሰቢያ መርሃ ግብር አካሂደዋል።

ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ፤ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት አሸባሪውን ህወሃት ከጠመንጃ አፈ ሙዝ በተጨማሪ በኢኮኖሚ አሻጥርና ሌሎች የጥፋት መንገዶች የከፈተውን የውጊያ አውደ ግንባር በጋራ በመመከት ለማሸነፍ መዘጋጀት አለብን ብለዋል።

የሰሜን ዕዝ ሰራዊት በትግራይ ክልል በነበረበት ወቅት የአገርን ዳር ድንበር ከመጠበቅ በተጓዳኝ በርካታ ህዝባዊ አገልግሎቶችን ሲሰጥ የቆየ የአገርና የህዝብ አለኝታ እንደነበር አስታውሰዋል።

ሆኖም "ወርቅ ላበደረ ጠጠር" እንዲሉ ሰራዊቱ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በአሸባሪው ህወሃት ክህደት ተፈፅጽሞበታል ብለዋል።

የሽብር ቡድኑ ከዚህ ድርጊቱ ሳይጸጸት መንግስት የወሰደውን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ወደ ጎን በመተው በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ በመፈጸም ጭካኔውን በንጹሃን ላይ አሳይቷልም ነው ያሉት።

በመሆኑም የሽብር ቡድኑ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ላይ የደቀነውን አደጋ ለመከላከል ኢትዮጵያዊያን ከየትኛውም ጊዜ በላይ በጋራ የምንቆምበት ጊዜው አሁን ነው ብለዋል።

"ሁሉም የሚሆነው በአገር ነው" ያሉት ሚኒስትሯ ሰራዊቱን በስንቅ፣ በትጥቅም ሆነ በሞራል መደገፍ የዛሬ ብቻ ሳይሆን የሁልጊዜም ስራችን ሊሆን ይገባዋል ነው ያሉት።

"እኛ በሰላም እንድንኖር ውድ ህይወቱን እየከፈለልን ያለውን የመከላከያ ሰራዊት በማንኛውም መንገድ ማገዝና መደገፍ ከሁላችንም ይጠበቃል" ብለዋል ዶክተር ፍጹም።

አሸባሪው ህወሃት በኢትዮጵያ ላይ ግልፅ ጦርነት የከፈተው በብዙ ግንባሮች በመሆኑ በየትኛውም አውደ ግንባር መክቶ ለማሸነፍ መዘጋጀት አለብን ብለዋል።

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በውጭ የሚያደርሰውን ጫና ለመቋቋም ከሚደረገው እንቅስቃሴ በተቃራኒ የኢኮኖሚ አሻጥር የሚፈጥሩ አካላት እንዳሉም አንስተዋል።

በመሆኑም የኢኮኖሚ ዘርፍ ተዋንያን ግንባር ላይ እንዳለው የመከላከያ ሰራዊት ለአገራቸው እየተዋደቁ መሆኑን በማሰብ ለትርፍ ብቻ ሳይሆን ለህዝባቸውም ግድ ሊላቸው ይገባል ብለዋል።

ህብረተሰቡ ሰርገው የሚገቡ ሽብር የሚፈጥሩና የሽብር ቡድኑን የሃሰት ፕሮፖጋንዳ የሚያራግቡ አካላትን በንቃት በመከተታተል ለህግ ማቅረብ አለበት ብለዋል።

አሸባሪው ህወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመውን ጥቃት አንደኛ ዓመት "አልረሳውም እኔም የኢትዮጵያ ሰራዊት ነኝ" በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም