ድርጅቱ ለወጣት ማዕከላትና ለጉባኤው 380 ሺህ ብር የሚገመቱ ቁሳቁሶችን በስጦታ አበረከተ

59
ደሴ ነሀሴ 13/2010 ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ የተባለው ድርጅት በደቡብ ወሎ ዞን ለወጣት ማዕከላትና ጉባኤዎች ማጠናከሪያ 380 ሺህ ብር የሚገመቱ ቁሳቁሶችን በስጦታ አበረከተ፡፡ የድርጅቱ አስተዳደር ኃላፊ ወይዘሮ ላቪ ደሴ በርክክብ ስነስርዓት ወቅት እንዳሉት ስጦታውን ያበረከቱት ከአሜሪካ አለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት/ዩ ኤስ ኤይድ/ እና ከፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ነው። ከስጦታዎች መካከል  በደሴና በኮምቦልቻ  ለሚገኙ የወጣት ማዕከላት የተለያዩ የስፖርት መጫወቻዎችና መዝናኛዎች የሚውሉ ቁሳቁሶች ይገኙበታል፡፡ እንዲሁም  ለደቡብ ወሎ ዞን፣ ለደሴ ከተማ፣ ወረባቦ፣ መቅደላ፣ ቃሉና ኮምቦልቻ ወረዳዎች የኃይማኖት ጉባኤዎች ለእያንዳንዳቸው የኮምፒውተርና ተጓዳኝ የመገልገያ ቁሳቁሶች ነው የተበረከው፡፡ የደሴ ከተማ ወጣቶች ማዕከል ስራ አስኪጅ ወጣት ደሳለኝ መኮንን ለማዕከላቸው የተበረከተው ስጦታ የነበረባቸውን የስፖርት ማዘውተሪያ ቁሳቁስ ችግር ለመፍታት እንደሚያግዝ ተናግሯል፡፡ የደቡብ ወሎ ኃይማኖቶች ጉባኤ ሊቀ መንበር ሊቀ መምህራን ብርሃነ- ህይወት እውነቱ በበኩላቸው የተደረገላቸው ድጋፍ የኃይማኖት ፎረሙ ስራውን ለማቀላጠፍ እንደሚረዳው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም