"የአሸባሪው ህወሓት ቡድን የከፈተውን የእብሪት ጦርነት ኢትዮጵያዊያን በተባበረ ክንድ ይመክቱታል'' - ኢዜአ አማርኛ
"የአሸባሪው ህወሓት ቡድን የከፈተውን የእብሪት ጦርነት ኢትዮጵያዊያን በተባበረ ክንድ ይመክቱታል''
ጥቅምት 24/2014 የአሸባሪው ህወሓት ቡድን በአገር ላይ የከፈተውን የእብሪት ጦርነት ኢትዮጵያዊያን በተባበረ ክንድ ይመክቱታል ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጄላ መርዳሳ ተናገሩ።
ሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማቱ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም አሸባሪው ህወሓት በሰሜን ዕዝ የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈፀመውን ጭፍጨፋ "አልረሳውም እኔም የኢትዮጵያ ሠራዊት ነኝ" በሚል መሪ ሃሳብ የመታሰቢያ መርሃ ግብር አካሂደዋል።
ሚኒስትሩ ቀጄላ መርዳሳ አሸባሪው ህወሓት እኔ ያልመራኋት አገር ትፍረስ በሚል ክፉ መንፈስ መጠነ ሰፊ ሠብዓዊ ቀውሶችን ሲፈጽም መቆየቱን አንስተዋል።
ከሁሉም የማይረሳው ግን ከሁለት ዓመት ዝግጅት በኋላ ቡድኑ ባሰለጠናቸውና ባስታጠቃቸው ግብረአበሮቹ በሰሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ክህደት ነው ብለዋል።
በአገር ህልውና ላይ የቃጣውን የእብሪት ጦርነት በመቀጠል በደረሰበት አካባቢ ሁሉ ሕዝብ እየጨፈጨፈና ከቤት ንብረቱ የሚያፈናቅል፣ ሕዝባዊ ዓላማ የሌለው የወረደ ቡድን ሆኗል ነው ያሉት።
ሚኒስትሩ ሽብርተኛው ቡድን የከፈተውን ጦርነት መላው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች በተባበረ ክንድ ይመክቱታል ብለዋል።
የሽብር ቡድኑ በውጭ ሃይሎች የገንዘብና የቴክኖሎጂ መረጃ እየታገዘ በተለያዩ አካባቢዎች ሁከትና ሽብር እየፈጠረ መሆኑን በመጥቀስ።
ዜጎች ለአገራቸው ወታደር መሆናቸውን በመገንዘብ አገር የማዳንና ብሄራዊ ጥቅምን የማስከበር ተልዕኳቸውን ከምንጊዜም በላይ ሊወጡ ይገባል ሲሉም ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ሕዝቡ በሽብር ቡድኑ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ሳይረበሽ ተረጋግቶ የአካባቢውን ሠላም ሊያስጠብቅ ይገባልም ብለዋል።
የሚኒስቴሩና የተጠሪ ተቋማት ሠራተኞች በመታሰቢያ መርሃ ግብሩ ለአገር መከላከያ ሠራዊት ደጀንነታቸውን ለማሳየት ደም ለግሰዋል።
ወጣቶቹ ኢትዮጵያን ከገጠማት ችግር ለማውጣት ሁሉም ወጣት ወደ ግንባር ከመዝመት ጀምሮ የሚጠበቅበትን ማድረግ አለበት ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።