ጀግኖች ሰማዕታትን የምንዘክረው የተሰዉለትን ዓላማ ለማስቀጠል በቁርጠኝነት ለመሰለፍ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ጀግኖች ሰማዕታትን የምንዘክረው የተሰዉለትን ዓላማ ለማስቀጠል በቁርጠኝነት ለመሰለፍ ነው
ሀዋሳ ፤ ጥቅምት 24/2014 ( ኢዜአ) አሸባሪው የህወሀት ቡድን የሰሜን ዕዝ ሰራዊት አባላት ላይ በፈጸመው ጥቃት የተሰዉ ጀግኖቻችንን የምንዘክረው የተሰዉለትን ዓላማ ለማስቀጠል በቁርጠኝነት ለመሰለፍ ነው ሲሉ የሲዳማ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተደድር ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ።
አሸባሪው የህወሀት ቡድን የሀገር አለኝታ በሆነው የሰሜን ዕዝ መከላከያ ሰራዊት ላይ ግፍ የተሞላበት ጥቃት የፈፀመበት አንደኛ ዓመት በሲዳማ ክልል ደረጃ በጧፍ ማብራትና በተለያዩ መርሀ-ግብሮች ታስቧል።
በመርሀ-ግብሩ ላይ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለጹት፤ ቅድሚያ ለሀገሩና ለወገኑ በሰጠው የመከላከያ ሰራዊት ላይ አሸባሪው ህወሀት የፈፀመበት ጭካኔ የተሞላበት ጭፍጨፋ የቡድኑን አረመኔያዊነት በገሀድ ያሳየ ነው።
ጀግኖች የሰራዊቱ አባላት ደም በከንቱ ፈሶ እንደማይቀር የተናገሩት አቶ ደስታ፤ የመስዋዕትነታቸውን ቀን የምናስበው የተሰዉለትን ዓላማና ተጋድሏቸውን ተቀብለን ኢትዮጵያን አፅንተን ለትውልድ ለማስተላለፍ በታላቅ ቁርጠኝነት በመሰለፍ ነው ብለዋል።
የሰራዊቱ አባላት ለሀገር የከፈሉት የሕይወት መስዋዕትነት በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ በወርቅ ቀለም ተፅፎ ከትውልድ ትውልድ እንደሚሸጋገር ገልጸዋል።
የብልጽግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሀም ማርሻሎ በበኩላቸው፤ የሽብር ቡድኑ ሰራዊቱን ከጀርባው በማጥቃት የሀገር ክህደት ተግባር ሲፈፅም በሥልጣን በነበረበት ወቅት ሲያራምድ የነበረውን ጭቆና ዳግም ለማስፈን መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ቡድኑ ሰርጎ በገባባቸው ክልሎች ላይ በንፁሀን ዜጎች ላይ አሰቃቂ ግድያ ፣ እንግልትና የንብረት ውድመት እያስከተለ እንደሚገኝ አውስተዋል።
ይህንን ሁኔታ መቀልበስና አባቶቻችን ሕይወታቸውን ገብረው ያቆዩልንን ኢትዮጵያን ማስቀጠል የሁላችንም ኃላፊነት ነው፤ የሽብር ቡድኑን ባጠረ ጊዜ ውስጥ መቅበር ይገባል ብለዋል።
የአሸባሪውን የጥፋትና መስፋፋት አባዜ በመግታት ከኢትዮጵዊያን ጫንቃ ላይ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማውረድ በሰው ኃይል ፣ በገንዘብና ቁሳቁስ ጭምር ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለማቅረብ እንደ ክልል በስፋት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች መካከል የሀዋሳ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ደረሰ ቡሳሮ በሰጡት አስተያየት ፤ የአካባቢውን ማህበረሰብ እንደቤተሰቡ በመቁጠር ዝቅ ብሎ በሚያገለግል ሰራዊት ላይ አሸባሪው ህወሐት ከጀርባው ጥቃት መፈፀሙ የክፋቱን ጥግ ያሳየበት መሆኑን ተናግረዋል።
የዚህን ቡድን ግብዐተ መሬት ለመፈፀም በሚደረገው ተጋድሎ ለመሳተፍ በማናቸውም ወቅትና ቦታ ሁሉ ለመሰለፍ ዝግጁ ነን ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የከተማው ፖሊስ እስከ መንደር ድረስ ካሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመቀናጀት የአካባቢውን ሠላም የማረጋገጥ ሥራ በንቃት እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የዛሬ ዓመት በአሸባሪው ቡድን በግፍ የተሰዉ ጀግኖች የሰሜን እዝ ሰራዊት አባላትን ለመዘከር በተካሄደው መርሀ ግብር ላይ ከሲዳማ ክልል፣ የወረዳና ከተማ አስተዳደር አመራሮች የተሳተፉ ሲሆን በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ውይይት አካሂደዋል።