"የትኛውንም ዋጋ ከፍለን አገራችን እና ሕዝቦቿን እናስቀጥላለን" - ኢዜአ አማርኛ
"የትኛውንም ዋጋ ከፍለን አገራችን እና ሕዝቦቿን እናስቀጥላለን"
ጥር 24/2014 (ኢዜአ) "የትኛውንም ዋጋ ከፍለን አገራችንን እና ሕዝቦቿን እናስቀጥላለን" ሲሉ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ተናገሩ።
የሚኒስቴሩ ሠራተኞችና የአመራር አባላት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በመከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ በአሸባሪው ህወሓት የተፈጸመውን ጭፍጨፋ አስበዋል።
ሠራተኞቹ ዕለቱን "አልረሳውም እኔም የኢትዮጵያ ሠራዊት ነኝ" በሚል መሪ ሃሳብ በማሰብ የህሊና ጸሎትና የሻማ ማብራት መርሃ ግብር አካሂደዋል።
ሚኒስትሯ ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ ሠራዊቱ ከሕዝቡ ጋር ክፉና ደጉን ያሳለፈ፤ የእናቴ ጓዳ ብሎ አብሮ የኖረ ሆኖ ሳለ በአሸባሪው ቡድን የተፈጸመበት ግፍ ታሪክ የማይዘነጋው ነው።
"ወራሪውና አሸባሪው የህወሓት ቡድን እኔ ካላስተዳደርኩ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን መኖር የለባቸውም ብሎ ከፍተኛ ዋጋ ማስከፈሉን ዛሬም ቀጥሏል" ነው ያሉት።
"ይህ እኩይ ዓላማ እንዲያከትም ከሁላችንም ብዙ ይጠበቃል" ያሉት ሚኒስትሯ የትኛውም ዋጋ ተከፍሎም ቢሆን ኢትዮጵያ መቀጠል አለባት ለዚህም ሁላችንም መዘጋጀት አለብን ብለዋል።
ሕመምን ለማስታመም አገር ያስፈልጋል፣ ለመወቃቀስም አገር ያስፈልጋል፤ በመሆኑም ለአገር ዘብ የምንቆም የኢትዮጵያ ሠራዊት መሆናችንን በተግባር ማረጋገጥ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
ሕዝቡ አካባቢውንና አገሩን በንቃት የመጠበቅ አገራዊ ሃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣም አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያዊያንን የመከፋፈል ሙከራዎችን መመከት የሁሉም ግዴታ መሆኑን ጠቁመው "ኢትዮጵያዊያን በሉዓላዊነታችን የማንደራደር መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል" ብለዋል።
የሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ሃላፊዋ ወይዘሮ ሩቂያ ሰኢድ በበኩላቸው መከላከያ ሠራዊቱ አገር ከመጠበቅ ባሻገር በማኅበራዊ መስኮች ከትግራይ ሕዝብ ጎን እንደነበር አስታውሰው በክህደት ከጀርባው መወጋቱ ትልቅ ሕመም ነው ብለዋል።
"የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሕመሙ ሕመማችን ነው፣ ጉዳቱ ጉዳታችን ነው፣ ምን ግዜም በማንኛውም ሁኔታ ከሠራዊቱ ጎን ነን" ሲሉ ተናግረዋል።