"ኢትዮጵያን ለማፍረስ የመጣውን ሃይል ቀብረን ክብሯን ከፍ እናደርጋለን" - ኢዜአ አማርኛ
"ኢትዮጵያን ለማፍረስ የመጣውን ሃይል ቀብረን ክብሯን ከፍ እናደርጋለን"
ጥቅምት 24/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን ለማፍረስ የመጣውን ሃይል በደምና በአጥንታችን ቀብረን የኢትዮጵያን ክብር ቀና እናደርጋለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ገለጹ፡፡
አሸባሪው ህወሃት የመከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝ አባላት ላይ የፈጸመው ክህደትና አሰቃቂ ጥቃት 1ኛ ዓመት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተገኙበት በመከላከያ ሚኒስቴር ቅጥር ግቢ ታስቧል።
"አልረሳውም! እኔም የኢትዮጵያ ወታደር ነኝ! " በሚል መሪ- ሃሳብ በተከናወነው መርሃ ግብር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልእክት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የመጣውን ሃይል በደምና በአጥንታችን ቀብረን የኢትዮጵያን ክብር ቀና እናደርጋለን ብለዋል።
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም አሸባሪው ህወሃት ሰራዊቱን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያና ህዝቦቿን ገድለዋል፤ ለማፍረስም ሰርተዋል ብለዋል።
በመሆኑም ዛሬም የኢትዮጵያ ልጆች ነን የምንል ሁላችንም አገርን ለመበተን፣ ለማዋረድ እና ክብሯን ለመግፈፍ የመጡትን ሃይሎች ችላ የማንል እና ድል የምንደርጋቸው ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የዛሬው ዕለትም በእኛ መስዋዕትነት የምትቀጥል አገር እንደምትኖር ቃል ኪዳን የምንገባበት ቀን ነው ብለዋል።
የአሸባሪው ስብስብ የራሱ ሃሳብ የሌለው፣ በሄደበት ህዝቡን ወሮ ዘርፎ የሚባላ ዘራፊ ሃይል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሁኑ ጊዜ ለራሱ በቀበሪያ የሚሆን ጉድጓድ በመቆፈር ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የአሸባሪው ስብስብ እየቆፈረ በሚገኘው ጉድጓድ የሚቀበርበት እንጂ ኢትዮጵያ የምትፈርስበት አይሆነም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያዊያን ጠላቶቻቸውን አዋርደውና ቀብረው ኢትዮጵያን ቀና ያደርጋሉ ሲሉ አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ በዘመናት መካካል በርካታ ጠላቶች ቢገጥሟትም ሁሉንም በድል አድራጊነት ተወጥታለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁንም በአንድነት ቆመን አገር ለማፍረስ የመጣውና አሸባሪ ቡድኑን እናሸንፋለን ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ነጻ እንስክትሆን ድረስ እያንዳንዱ ዜጋ " እኔም የኢትዮጵያ ወታደር ነኝ " በማለትና ከሰራዊቱ ጎን በመቆም ይህን ጠላት በመመከት እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡
ሰራዊቱ ሁኔታዎች ባልተሟበት ሁኔታ አገሩን ለመከላከል እንደ ሻማ በመቅለጥ ላይ ይገኛል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እያንዳንዱ ወጣት ሰራዊቱን በመቀላቀል አገሩን ማዳን እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
እያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍልም ያለውን አስፈላጊ በመሆነበት ሁሉ ያለውን ትጥቅ ለመከላከያው በመስጠት ጠላትን ለመደምሰስ የራሱን አሻራ ማኖር እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡
አንድነታችንን ጠብቅን በውስጥም በውጭም የገጠሙንን ጠላቶች እናሸንፋለን ሲሉም አረጋግጠዋል፡፡
አሸባሪው ህወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመውን ጥቃት አንደኛ ዓመት "አልረሳውም እኔም የኢትዮጵያ ሰራዊት ነኝ" በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ነው።