የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የውሳኔ ሀሳብ እንደግፋለን - ኢዜአ አማርኛ
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የውሳኔ ሀሳብ እንደግፋለን
ነገሌ ፤ ጥቅምት 24/2014 (ኢዜአ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሀገር ለማዳንና የህግ የበላይነትን ለማስከበር ለደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊነት የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ በጉጂ ዞን የነገሌ ከተማ ነዋሪዎች አስታወቁ፡፡
አሸባሪው የህወሓትና ተላላኪዎቹ ሀገር ለማፍረስ ያነገቡትን እኩይ ዓላማ ንጹሃን ዜጎችን በግፍና በጭካኔ የመግደል ተግባራቸውን ገፍተውበታል።
የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ አሸባረውን ህወሓት ከነግብረ አበሮቹ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ ሁሉን አቀፍ ትግል እያደረጉ ነው።
አሸባሪዎቹን ለማስወገድ እየተካሄደ ላለው ትግል ስኬት ለጀግናው መከላከያ ሰራዊት ደጀን ከመሆን አልፈው አካባቢያቸውን በንቃት እንዲጠብቁ ከመንግስት ጥሪ ተላልፏል።
ለዚህም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመላ ኢትዮጵያ ተግባራዊ እንዲደረግ ውሳኔ አሳልፏል።
ይህን ተከትሎ ኢዜአ ያነጋገራቸው የነገሌ ከተማ ነዋሪዎች እንደገለጹት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ይደግፋሉ፤ ለተግባራዊነቱ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ይወጣሉ።
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ጥላሁን ዋሬ ፤ የውሳኔ ሀሳቡ ቢዘገይም የሽብር ጥቃትን ለመከላከል ወሳኝ በመሆኑ ለተፈጻሚነቱም ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡
አስተያየት ሰጪው እንዳሉት፤ የሽብር ጥቃቱ ማንንም ያለየና ሀገር የሚያፈርስ እኩይ ተግባር በመሆኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ የሕዝቡን ድጋፍ፣ አንድነትንና ትብብርን ይጠይቃል፡፡
በመሆኑም ለአዋጁ ተፈጻሚነትና ለህግ የበላይነት መከበር ሁላችንም መረጃ የመስጠት፣ ሽብርተኞችን የመጠቆምና የማጋለጥ ኃላፊነት አለብን ብለዋል፡፡
ሽብርተኛው ህወሓት የውጭ ዜጎችን ጭምር ለጦርነት በማሰለፍ የእናት ጡት ነካሽነቱን በተግባር እያረጋገጠ ቡድን ነው፡፡
ሌላው ነዋሪ አቶ ተፈራ ብርቄ በበኩላቸው፤ እንዳሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሽብር ጥቃትን በመከላከል የዜጎችን ስደትና መፈናቀል ያስቀራል የሚል ተስፋ አላቸው፡፡
ሀገር ለማፍረስ የውጭ ጫናና ተፅዕኖን እንደ መልካም አጋሚ የተጠቀሙ የሽብር ቡድኖች እኩይ ዓላማ አይሳካም በሕዝባዊ አንድነት ይከሽፋል፡፡
በተሳሳተ መረጃ ንፁሃን እንዳይጎዱ ለመንግሥትና ለፀጥታ ኃይሉ የተጣራና በማስረጃ የተደገፈ ጥቆማ በመስጠት የድርሻቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።
ሽብርተኞችን የሚደግፍና ሀገር የሚያፈርስ የውጭ ጫናና ተፅእኖ ከመቋቋም ሌላ ምርጫ የለንም ያሉት ደግሞ አቶ ቦኮና ሀወዝም ናቸው።
ሀገር ለማዳን የመተባበር፣ ፀጉረ ልውጦችን የመጠቆም፣ በደጀንነት መከላከያ ሠራዊቱን የመደገፍ፣ የሕልውና እና የዜግነት ግዴታ ውስጥ ገብተናል ብለዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሀገር የማዳንና የሽብር ጥቃትን የመከላከል ዓላማ እንዲሳካ የመንግሥትን መመሪያ በማክበርና በማስከበር የበኩላቸው አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ነው ነዋሪዎቹ የገለጹት፡፡
መንግሥት የሀገርን ህልውና፣ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን ከውስጥና ከውጭ ጠላቶች የመጠበቅ የሕግ፣ የሞራል ኃላፈነትና ግደታ ስላለበት ያወጣው አዋጅ ትናንት ለህዝብ ይፋ መደረጉ ይታወሳል።