ቀጥታ፡

አሸባሪው ህወሃት በተከፋዮቹ በኩል 24 ሰአት የውሸት መረጃ እያሰራጨ ነው

ጥቅምት 24/2014(ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት ተከፋዮቹ የውጭ ዜጎች 24 ሰአት የውሸት መረጃ ማሰራጨቱን አጠናክሮ መቀጠሉን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አንድ የሶሾሎጂ ምሁር ተናገሩ።
በኢትዮጵያ ደረጃ የሚታየው የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ታስቦበት፣ በዕቅድ፣ በባለሙያ፣ በበጀት፣ በድርጅት፣ በመታገዝ የሚከናወን የዘመኑ የዲጂታል ጦርነት መሆኑን በርካቶች ይናገራሉ።

የአሸባሪው ህወሃት ባለስልጣናትና አጋሮቻቸው በአንዳንድ ምዕራባውያን የሚዲያ ተቋማትንና በሰብአዊ መብትና ለጋሽ ድርጅቶች የሚሰሩ የውጭ ዜጎችን በመጠቀም 24 ሰአት ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨቱን ቀጥለውበታል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሶሾሎጂ ዲፓርትመንት መምህርና ተመራማሪው ፕሮፌሰር ጌትነት ታደለ፤ አሸባሪው ህወሃት ህዝብ ለማደናገር በተከፋዮቹ የውጭ ዜጎች የውሸት መረጃ እያሰራጨ መሆኑን ይናገራሉ።

በመሆኑም የውጭውም ማህበረሰብ ይሁን የኢትዮጵያ ህዝብ የአሸባሪውን የተለመደ ቅጥፈት በመረዳት በውሸት ዘገባዎች ሊደናገር አይገባም ብለዋል።

በተለይም አሁን ላይ የአሸባሪው ህወሃት ተከፋይ የውጭ ዜጎች በተደራጀ መልኩ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ በማሰራጨት ላይ መጠመዳቸውን ጠቅሰው ሁላችንም በጋራ ልንመክታቸው ይገባል ነው ያሉት።

ህግ የማስከበር ስራው ከተጀመረ ወዲህ የተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች በተለያዩ አለም አቀፍ ሚዲያዎች በመጋበዝ የህወሃትን የጥፋት አጀንዳ እና መንግስት እየወሰደ ያለውን ሀገር የማዳን እርምጃ በተመለከተ ሲሰጡት የነበረው መረጃ የሚበረታታ መሆኑንም ፕሮፌሰር ጌትነት ጠቅሰዋል።

 የሐሰት መረጃዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ1 ሺህ  እስከ 100 ሺህ ሰዎች ተደራሽ ሲሆኑ የእውነተኛ መረጃ ስርጭት ግን ከ1 ሺህ  ሰዎች በላይ እንደማይዘል ጥናቶች ይጠቁማሉ።

አንድ ሐሰተኛ መረጃ በቅጽበት ለ1 ሺ 500 ሰዎች ዘንድ ሲደርስ አንድ እውነተኛ መረጃ ግን በስድስት እጥፍ ዘግይቶ መሆኑ ይነገራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም