የመከላከያ ሰራዊትን ማጠናከር ኢትዮጵያን ማጠናከር ነው፤ በሰራዊቱ ላይ የሚደረግ ጥቃት ደግሞ የሀገር ክብርን መድፈር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመከላከያ ሰራዊትን ማጠናከር ኢትዮጵያን ማጠናከር ነው፤ በሰራዊቱ ላይ የሚደረግ ጥቃት ደግሞ የሀገር ክብርን መድፈር ነው
ጥቅምት 24/2014(ኢዜአ) "የመከላከያ ሰራዊትን ማጠናከር ኢትዮጵያን ማጠናከር ነው፤ በሰራዊቱ ላይ የሚደረግ ጥቃት ደግሞ የሀገር ክብርን መድፈር ነው" ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አደም ፋራህ ገለጹ፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት ሰራተኞችና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች አሸባሪው ህወሃት በመከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ አባላት ላይ የፈጸመውን ክህደትና ጥቃት 1ኛ ዓመት ሻማ በማብራት አስበዋል፡፡
የፓርቲው ዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ፤ የመከላከያ ሰራዊት በሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተዋቀረ የሀገር አንድነት ምልክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ሰላምና ደህንነት የህይወት መስዋትነት የሚከፍል መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ጥቃት መፈጸም በሁሉም ኢትዮጵያውያን ላይ ጥቃት መፈጸም መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ አሸባሪው ህወሃት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ አባላት ላይ የፈጸመውን ጥቃት መቼውንም እንረሳውም ብለዋል፡፡
የመከላከያ ሰራዊቱን ማጠናከር ኢትዮጵያን ማጠናከር ነው፤ ለሰራዊቱ ክብር መስጠት ደግሞ የሀገር ወዳድነት ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም የሰራዊት ከራስ በፊት ለህዝብ የመቆም ክብር በተግባር የሚረጋገጥበት መሆኑን ተናግረው፤ ኀብረተሰቡ የመከላከያ ሰራዊቱን ከመደገፍ ባሻገር የሰራዊቱ አካል መሆን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
የመከላከያ ሰራዊቱ ጥንካሬ የሚረጋገጠው በሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተሳትፎ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ከዚህ አኳያ በተለይ ወጣቶች የመከላከያ ሰራዊቱን በመቀላቀል ሀገራቸውን ማጠናከር እንዳለባቸውም አቶ አደም ፋራህ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ይህን በማድረግም አሸባሪውን ህወሃት ጨምሮ ሌሌች የኢትዮጵያን ህልውና የማይፈልጉ ኃይሎችን ማሸነፍ እንደሚቻል አብራርተዋል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈ ቤት ሰራተኞች ከደሞዛቸውን ጨምሮ ሰራዊቱን በተለያየ መልኩ እየደገፉት መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይ ድጋፉን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡
አሸባሪው ህወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመውን ጥቃት አንደኛ ዓመት "አልረሳውም እኔም የኢትዮጵያ ሰራዊት ነኝ" በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ነው።