ቀጥታ፡

በአገር የማዳን ዘመቻው ኢዜአ የመገናኛ ብዙሃን ሰራዊት ሆኖ ይቀጥላል

ጥቅምት 24/2014 በአገር የማዳን ዘመቻው ኢዜአ ከፀጥታ ሃይሉ ጎን በመሰለፍና መረጃ ለህዝብ ተደራሽ በማድረግ የመገናኛ ብዙሃን ሰራዊት ሆኖ የሚቀጥል መሆኑን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ሰይፈ ደርቤ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሰራተኞች አሸባሪው ህወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመውን ጥቃት አንደኛ ዓመት በማስመልከት የመታሰቢያ መርሃ ግብር አካሂደዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የኢዜአ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሰይፈ ደርቤ፤ ኢትዮጵያ የገጠማትን ወቅታዊ ችግር በአሸናፊነት እንድትሻገር ሁላችንም በተሰማራንበት የሙያ መስክ በብቃትና በንቃት መወጣት ይጠበቅብናል ብለዋል።

በአገር የማዳን ዘመቻው እስካሁንም የኢዜአ ሰራተኞች ከፀጥታ ሃይሉ ጎን በመቆም በየአውደ ግንባሮቹ በመገኘት መረጃዎችን ለህዝብ ተደራሽ በማድረግ "የመገናኛ ብዙሃን ሰራዊት" መሆናቸውን በተግባር አሳይተዋል ብለዋል።

አሸባሪው ህወሃት በመከላከያ ሰራዊትና  በህዝቦች እንዲሁም በአገር ላይ ውድመት በማድረስ የሚፈፅመውን ግፍና በደል ኢዜአ ለህዝቡ ብሎም ለመላው ዓለም ተደራሽ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው አሁንም ይህንኑ ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ኢትዮጵያን ለማፍረስ እስከ ሲኦል እገባለሁ ብሎ ከውስጥና ከውጭ ሃይሎች ጋር እየሰራ ያለው አሸባሪው ህወሃት እስከወዲያኛው እስከሚወገድ የኢዜአ ሰራተኞች የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ግዴታ ለመወጣት መዘጋጀታቸውንም ዋና ስራ አስፈፃሚው አረጋግጠዋል።

በዚህ አገር የማዳን ዘመቻ ኢትዮጵያን አሸናፊ ለማድረግ ሁሉም በየሙያ መስኩ ተጨማሪ ጊዜ ሰጥቶ በሃላፊነትና በቁርጠኝነት መስራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የአገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ በአሸባሪው ህወሃት ጥቃት የተፈፀመበትን 1ኛ ዓመት ስናስብ ኢትዮጵያ ላይ የተነሱ ጠላቶችን በጋራ ሆነን ለመመከት በመዘጋጀት መሆን አለበት ብለዋል።

ለኢትዮጵያ ሰላምና ሉአላዊ አንድነት ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታችንን አጠናክረንና ክንዳችንን አበርትተን መሆን አለበት ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የአገር መከላከያ ሰሜን እዝ በአሸባሪው ህወሃት ጥቃት የተፈፀመበት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ እንደነበር  ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም