ቀጥታ፡

አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን ለመበታተን የሚጠቀምበትን የሃሰት ትርክት ቀጥሎበታል

ጥቅምት 24/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህውሃት ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት የኢትዮጵያን አንድነት ለማጥፋት ሲጠቀምበት የነበረውን የሃሰት ትርክት አሁንም ጦርነት ከፍቶ ቀጥሎበታል ሲሉ የህግና ታሪክ መምህሩ ዶክተር አልማው ክፍሌ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማህበር ዋና ጸሃፊና የህግና ታሪክ መምህሩ ዶክተር አልማው ክፍሌ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ ከኢዜአ ጋር በስልክ ቆይታ አድርገዋል።

በንግግራቸውም የህወሃት አሸባሪ ቡድን የስልጣን ዘመኑን ለማራዘም ከሚጠቀምባቸው ተግባራት አንዱ የሃሰት ትርክት መሆኑን አስታውሰዋል።

የአሸባሪው የሃሰት ትርክት ህዝብን ለመለያየት፣ ትኩረት ለማስቀየር፣ ለማሸበር እንደ አጠቃላይ ኢትዮጵያዊ አብሮነት ችግር ላይ እንዲወድቅ ለማድረግ መሆኑን አብራርተዋል።

የነበረችውን ኢትዮጵያ በማጥፋት የህወሃት የበላይነት የሚንጸባረቅባትን አገር ለመፍጠር የያዙትን እቅድ ለማሳካት የህዝብ አንድነትን ማፍረስ ዋነኛ ትኩረታቸው መሆኑንም አስረድተዋል።

የሃሰት ትርክትንና የመከፋፈል ሴራ በትምህርት፣ በምጣኔ ሃብት፣ በፖለቲካ፣ በማህበራዊ ግንኙነት ውስጥ በማካተት ለማስረጽ መስራታቸውንም ዶክተር አልማው ጠቅሰዋል።

አሸባሪው ህወሃት በኢትዮጵያ ያልነበረ እንዲሁም የተዛባ ታሪክ በማሰራጨት በህዝብ ዘንድ ጥርጣሬና ግጭት እንዲፈጠር አጀንዳ ቀርፆ ሲሰራ የኖረ አገር አፍራሽ ሃይል መሆኑንም ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሃት ሲፈጠርም ኢትዮጵያን ለማፍረስና ህዝቦችን ለመለያየት አስቦ በመሆኑ በየትኛውም ጊዜ ከውሸትና ማጭበርበር ሊጸዳ እንደማይችል ዶክተር አልማው አስረድተዋል።

ለህዝብ ሳይሆን ለራሳቸው ጥቅም የሚያቆሟቸው የታሪክ መታሰቢያዎች ህዝብን የሚጠቅሙ ሳይሆኑ ጥላቻን የሚያጭሩ እንደነበሩም አስታውሰዋል።

የሽብር ቡድኑ ኢትዮጵያን ለማፍረስ በሌሎች አገሮች ተሞክሮ ውጤታማ የሆነውን አብዮታዊ ዴሞክራሲ ተግባራዊ በማድረግ መስራቱንም አስረድተዋል።

አብዮታዊ ዴሞክራሲ የገዳይ ተገዳይ፣ አሳዳጅ ተሳዳጅ፣ የቀማኛ ተቀሚ ትርክትን በመያዙ አንዱ ብሔር በሌላው ላይ እንዲነሳ የፈጠራ ታሪኮችን ተጠቅሞ በተለያዩ መንገዶች ህዝብን ያደናገረ ርእዮተ ዓለም እንደነበርም አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም