ሀገር ለመበተን የተነሳውን የህወሓት የሽብር ቡድን ለመደምሰስ ተዘጋጅተናል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገር ለመበተን የተነሳውን የህወሓት የሽብር ቡድን ለመደምሰስ ተዘጋጅተናል
ደብረ ብርሃን (ኢዜአ) ጥቅምት 24/2014 የክተት ጥሪውን ተቀብለው ሀገር ለመበተን ቆርጦ የተነሳውን የህወሓት የሽብር ቡድን ለመደምሰስ መዘጋጀታቸውን የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ነዋሪዎቹ በሀገር ሉአላዊነት እንደማይደራደሩ ለኢዜአ አስታውቀዋል ።
በደብረ ብርሃን ከተማ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት የድጋፍና የልማት ማህበር ምክትል ሰብሳቢ መቶ አለቃ ወንድወሰን ግዛው ኢትዮጵያ በጀግኖች አባቶች ደም ተከብራ የቆየች መሆኑን ገልጸዋል።
''ህዝቦቿ ለዘመናት ተዋደንና ተከባብረን የኖርንባት ሀገራችን አሁንም እኛ ልጆቿ እያለን በወራሪውና ጨፍጫፊው የህወሓት ቡድን አትደፈርም'' ብለዋል።
ሽብርተኛው ህወሓት በሀገርና በዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን በደል፣ ዘግናኝ ግፍና ዝርፊያን ለመግታት የመንግስትን የክተት ጥሪ መቀበላቸውን ተናግረዋል።
''ሀገራችን ደማችን ነች'' ያሉት መቶ አለቃ ወንደወሰን፣ በሀሃገር ሉአላዊነት ላይ እንደማይደራዱና ለህዝብ ሰላምና ለሀገር ክብር ሲሉ ምንም አይነት ዋጋ ለመክፈል መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።
የማህበሩ አባላት በልምዳቸው የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ለማገዝ ከክተት ጥሪው በፊት ጥያቄ በማቅረብ ራሳቸውን ሲያዘጋጁ መቆየታቸውን ጠቁመው ገሚሶችም በግንባር ዘምተው የጥፋት ቡድኑን እየተፋለሙ መሆኑን ገልጸዋል።
አሁንም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የኢትዮጵያ መዥገር የሆነውን አሸባሪና ጨፍጫፊ ቡድን በመደምሰስ የኢትዮጵያን ክብር ለመመለስ አባላቱ የክተት ጥሪውን ተቀብለው ወደ ግንባር ለመዝመት መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል።
የውጭ ቅጥረኛና ተላላኪ የህወሓት ቡድን ሀገር የመበተን ህልም በኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ ለመደምሰስ የክልሉን መንግስት የክተት ጥሪ መቀበላቸውን የገለጹት ደግሞ አቶ ደምሰው ዘለቀ ናቸው።
በወንበዴው ትህነግ ሀገር ስትተራመስና ስትፈርስ ከማየት በላይ አሳፋሪ ነገር እንደሌለ ጠቁመው "እጅን አጣጥፎ በመቀመጥ የአሸባሪውን የሞት ድግስ አንጠብቅም፤ ክተት ጥሪውን ተቀብለን ለመዝመት ተዘጋጅተናል" ብለዋል።
"አሸባሪው የህወሓት ቡድን ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲሁም ለሰላም ግንባታ ጉልህ ድርሻ ያላቸውን ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ተቋማት፣ ቤተ እምነቶችና ሀገራዊ እሴቶቻችን ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው በደል ፈጽሟል" ያሉት ደግሞ በከተማው የደብረ ኢጳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር አየለ ግዛቸው ናቸው።
"ቡድኑ የህዝቦችን እሴቶች ከማውደም በላይ ሃገሪቱ ከማትወጣበት የኢኮኖሚ አዘቅት ውስጥ ከቷት ለማለፍ እየፈጸመ ያለውን የጥፋት ተግባር በተባበረ ክንድ ለማስቆም እንሰራለን" ብሏል።
"የመማር ማስተማር ስራውን ማከናወን የሚቻለው ሀገር ስላም ስትሆን በመሆኑ በክተት ጥሪው መሰረት ለመዝመት ተዘጋጅቻያለሁ" ብለዋል።
በአማራ ክልላዊ መንግስት የአሸባሪውን የህወሓት ቡድን የጥፋት ተግባር ለመግታትና የህዝብን ደህንነት ለማስጠበቅ የክተት ጥሪ መታወጁ ተከትሎ ዜጎች ተግባራዊ ምላሽ መስጠት ጀምረዋል።