ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሳውን አሸባሪ ለመደምሰስ ተነስተናል

ባሕር ዳር፤ ጥቅምት 23/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን አፍርሶ አማራን ለማዋረድ የተነሳውን አሸባሪ ለመደምሰስ በግንባር ቀደምነት እንሰለፉለን ሲሉ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ያተኮረ የንቅናቄ መድረክ ውይይት ዛሬ አካሄደዋል።  

ነዋሪዎቹ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ኢትዮጵያን አፍርሶ አማራን ለማዋረድ የተነሳውን አሸባሪውን ህወሓት ለመደምሰስ በግንባር ቀደምትነት ይሰለፋሉ።

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ በቃሉ ዋለልኝ እንደገለጹት አሸባሪ ህወሓት ኢትዮጵያን አፍሶ የአማራን አንገት ለማስደፋት እኩይ ዓላማውን ካነገቡ ከግብረ አበሮቹ ጋር እየተንቀሳቀሰ ነው።

''እኔም እንደ አንድ ዜጋ አሸባሪ ቡድኑን ለመደምሰስ መንግሥት በጠራው የክተት ዓዋጅ መሰረት በምችለው ልክ ለመፋለምም ሆነ በደጀንነት ለማገልገል ዝግጁ ነኝ'' ብለዋል።

ቀደም ሲልም የከተማዋን ነዋሪዎች በማስተባበር ለመከላከያ ሠራዊት፣ ለአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሺያና ለፋኖ የሚሆን ድጋፍ ማሰባሰባቸውንም አስታውሰዋል።

በተለይ ወጣቶች የክተት ዘመቻውን ጥሪ ተቀብለው በመዝመት የአሸባሪውን እኩይ ዓላማ በማምከን ሀገራቸውን እንዲታደጉም ጠይቀዋል።

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ወጣት ቤንጃሚን ወንዴ በበኩሉ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከተደራጁ መሰል ቡድኖች ጋር ሌት ተቀን እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

አሸባሪው ህወሓት በየደረሰበት ንጹሃንን በመግደል፣ ንብረት በመዝረፍ፣ የእምነት ተቋማትን በማውደምና አስነዋሪ ተግባራትን በመፈፀም ኢትዮጵያን አፍርሶ አማራን የማዋረድ አቋሙን በተግባር እንያሳየ ነው።

በመሆኑም አሸባሪውን የህወሓት ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ ቆርጬ ተነስቻለሁ ብሏል።   

''አንድ ጊዜ እንጂ፤ ሁለት ጊዜ ሞት ባለመኖሩ ሀገሬን ከብተና ለመታደግ ግንባር ድረስ ሄጄ መክፈል የሚገባኝን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ'' ሲልም አቋሙን ገልጿል።

"በወገኖቻችን ላይ ግፍ እየፈፀመ ያለውን ወራሪው ኃይል ለመደምሰስ የምሰስተው ጉልበት የለኝም'' ያሉት ደግሞ ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ መልካም ፋሲል ናቸው።

ሀገርን የማዳን ጥሪውን ተቀላቅለው ለመዝመት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው፤ ጓደኞቻቸውም የእሳቸውን ፈለግ ተከትለው ትግሉን እንዲቃላቀሉ ይቀሰቅሳሉ።

ጠላትን በመፋለምም በግንባር ለሚፋለሙት ምግብና ውሃ በማቅረብ ለሕልውና ዘመቻው ስኬት የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ  ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው ነዋሪዎቹ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ በደልና ግፍ እየፈፀመ ያለውን አሸባሪውን ህወሓት ለመደምሰስ ግንባር ቀደም ተሰላፊ መሆን እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

በከተማዋ መሳሪያ የታጠቁ ጠላትን በግንባር እንዲፋለሙ፣ አቅም የሌላቸው መሳሪያቸውን አቅም ላለው እንዲሰጡ በተወሰነው መሰረት ምዝገባ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።

በመድረኩ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም