የህወሓት አሸባሪ ቡድን እስከወዲያኛው ካልጠፋ አገርና ሕዝብ ሠላም አያገኙም - ኢዜአ አማርኛ
የህወሓት አሸባሪ ቡድን እስከወዲያኛው ካልጠፋ አገርና ሕዝብ ሠላም አያገኙም
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) የህወሓት አሸባሪ ቡድንን እስከመጨረሻው ማጥፋት ካልተቻለ አገርና ሕዝብ ሠላም ሊያገኙ አይችሉም ሲሉ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ትዴፓ/ ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ ተናገሩ።
ዶክተር አረጋዊ አሸባሪው ህወሓት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈፀመው ግፍ እና ጭፍጨፋ ለረዥም ጊዜ ኢትዮጵያን ለማፍረስና ለማተራመስ አቅዶ ሲሰራ መቆየቱን ያሳያል ብለዋል።
ከዚህም በላይ አሸባሪ ቡድኑ ለኢትዮጵያ ሕዝብና አንድነት የማይበጅ፤ በተለይም ለትግራይ ሕዝብ ያልቆመና ሠላምን የማይሻ መሆኑን አሁንም በሚፈጽማቸው የጭካኔ ተግባራቱ በተጨባጭ አሳይቷል ነው ያሉት።
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ሠራዊት አባላት ላይ የፈፀመው የጭካኔ ተግባር ቡድኑ የስልጣን ጥሙን ለማርካት የማይፈጽመው እኩይ ተግባር እንደሌለ በግልጽ የሚያመላክት እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ይህን እኩይ ተግባሩን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ለ27 ዓመታት ሲፈጽመው የቆየ ነው ያሉት ዶክተር አረጋዊ በሠራዊቱ ላይ የፈፀመው ድንገተኛ ጭፍጨፋም 'አፀያፊና አስቀያሚ' ሲሉ ተናግረዋል።
"ቡድኑ ሕዝብ ለማበጣበጥና አገር ለማተራመስ ተግቶ የሚሰራ በመሆኑ በጋራ በመሆን ለአንዴና ለመጨረሻ እንዲጠፋ ማድረግ ይገባል" ብለዋል።
ትዴፓ የሽብር ቡድኑ በተለይ በአማራና በአፋር ክልሎች ሕዝቦች ላይ እየፈፀመ ያለውን የጭካኔ ተግባር እንዳይቀጥል በማያዳግም መልኩ ሥርዓት ማስያዝ ይገባል የሚል እምነት እንዳለውም ተናግረዋል።
ህወሓት ባለፉት 47 ዓመታት የሕዝብ መብት አክብሮ የማያውቅ መሆኑ የሚታወቅ ነው ያሉት ዶክተር አረጋዊ የኢትዮጵያን እድገት ከማይፈልጉ የውጭ ኃይሎች ጋር በማበር አገሪቷን ለማፈራረስ ተግቶ እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
በመሆኑም ይህንን የጥፋት ኃይል ዳግመኛ እንዳያንሰራራ በማድረግ ረገድ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጋራ መስራት ምርጫ የማይገኝለት ተግባር ሊሆን እንደሚገባው አመልክተዋል።
የህወሓት አሸባሪ ቡድን እንደገና ለመደራጀትና ለማንሰራራት የሚያደርገው ሙከራ የአገሪቷን ሃብት የመበዝበዝና ሕዝቡን ዳግም ወደ ጭቆናና ባርነት ለመለስ ያለውን ፍላጎት የሚያሳይ ነው ብለዋል።