ቀጥታ፡

ጥቅምት 24 በኢትዮጵያ ላይ ክህደት በአለኝታዋ ላይ ግፍ

“ለወገን ክብር ለሀገር ዳር ድንበር ራሱን በቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ 20 ዓመታት ቀብሮ የኖረ የኢትዮጵያ አለኝታ በራሱ ሰዎች በሚሞትላቸው ዜጎች የተካደበት፤ ግፍ የተፈጸመበት እና የተሰዋበት ዕለት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም።በተለያዩ አካባቢዎች የአንበጣ መንጋ አጋጥሞ የደረሰ ሰብል እንዳይወድም እና ረሀብ እንዳይከሰት አንበጣው ከሚፈለፈልብት አካባቢ ለመቆጣጠር በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ርብርብ ሲደረግ ነበር።

ህዝብን ከረሀብ አደጋና ከእህል ውድመት ለመከላከል የኢትዮጵያ ደጀን የሆነው የአገር መከላከያ ሠራዊትም ደጀንነቱን ለማሳየት ማጭድ ይዞ ማሳ ገብቷል።በኢትዮጵያ ጥላቻ ጫካ ገብተው፣ በህዝብ ደም ከጫካ ወጥተው፣ ስልጣን ላይ የነበሩ ኋላም ግፍ፣ ባርነትና ብዝበዛን መሸከም ባቃተው ህዝብ እምቢተኝነት ከስልጣን የተባረሩ የኢትዮጵያ ጠላቶች ግን በመሸጉበት ትግራይ ክልል ዋሻ ሆነው ሀገሪቷን ለመበተን ሲዶልቱ ነበር።

ሠራዊቱ የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ሲሰጥ፤ አንበጣን ሊያጠፋ ሲሰማራ ጠብቆኛል ከልሎኛል ያላሉ፣ ከታሪክ ያልተማሩ፣ ሀገር ሻጭ አንበጣዎች ግን አገር ለማፍረስ ወረራ ጀመሩ።የአሸባሪው ህወሃት አባላት በደም በታጠበ እጃቸው ሀገርን የመበተን ዱለታቸውን ሲያቀነቀኑ፣ ጦር አውርድ ሲሉ ሦስት አመታትን ቢያሳልፉም 20 ዓመታትን በጋብቻ እና እራስን በመሰዋት የተጋመዳቸው ሠራዊት ላይ ግን ግፍ ይፈጽማሉ ብሎ የጠበቀ አልነበረም።

ይልቁንም ከቀናት በፊት የደረሰ ሰብል በአንበጣ መንጋ እንዳይበላ ከገበሬው ጋር ሲሰበስብ በነበረ የህዝብ ልጅ በሆነው መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ይፈጸማል፣ ይካዳል ብሎ የገመተ አልነበረም።የክህደቱ ጅማሬ ግን ከግምትም በላይ ሆኖ አንገት ያስደፋል። ለአንድ አላማ ለአንድ ሀገር ሉዐላዊነት መጠበቅ ከተሰባሰቡት የመከላከያ ሠራዊት አባላት መካከል በስልጣን ላይ የነበሩ እና በአባልነት በሰራዊቱ ውስጥ የሚገኙ እና የትግራይ ክልል ሚሊሻዎች የሰራዊቱ አባላት እራት ተመግበው በተኙበት የጥይት አረር አዘነቡባቸው።

ይህንንም ድርጊት የአሸባሪው ህወሃት ቃል አቀባይ የነበረው ሴኮቱሬ ጌታቸው “በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ መብረቃዊ ጥቃት ፈጽመናል” ሲል በሰራዊቱ ላይ የፈጸሙትን ግፍ እና በሀገር ላይ ያደረሱትን ክህደት በአደባባይ መስክሯል።መብረቃዊ ከተባለው ጥቃት ጀምሮ እንኳን ወገን በሆነ ሰራዊት ላይ ቀርቶ በጠላትነት በተፈረጀ አካል ላይ ሊፈጸም ይችላል የማይባል ግፍ በመከለከያ ሠራዊቱ ላይ ተካሂዷል።

አብሮ በኖረ ጓደኛ ጥይት ከመመታት እስከ ብሔር ለይቶ ግድያና የቡድን ርሸና ድረስ በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ የተፈጸሙ የግፍ ድርጊቶች፣ የእናት ጡት ንክሻዎች ናቸው።ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በኋላ ለ20 ዓመታት በትግራይ ክልልና በድንበር ላይ በነበረው የሰሜን እዝ ሠራዊት ላይ የተፈጸመው ግፍ የአሸባሪው ህወሃት ሃይሎች መሳሪያ ለመዝረፍ በሚል ሰበብ ቢሸፍኑትም ወደ ጅምላ ግድያና ዘር ተኮር ጥቃት መቀየሩን ጥቃቱን ተከትሎ በተካሄደ ምርመራ ተረጋግጧል።

በዕዙ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ አመራሮችም የሰራዊቱን አባላት በማታለል የታቀደው የአገር ክህደት ተግባር እንዲሳካ ማድረጋቸውን ጥቃቱን በታላቅ ጀበዱ ያከሸፉና ከጥቃቱ የተረፉ የሠራዊቱ አባላት መስክረዋል።

ትምህርት ቤትና የህክምና ተቋማትን በመገንባት፣ የግብርና ስራዎችን በአርሶ አደሩ ማሳ ተገኝቶ በማገዝ እንዲሁም በሌሎች ማህበረሰባዊ ድጋፎች አለኝታነቱን ሲያሳይ በነበረ ሰራዊት ላይ ‘ባጎረስኩ እጄን ተነከስኩ’ ከሚባለው በላይ በከሐዲው የህወሃት አሸባሪ ቡድን ሰራዊቱ የከፋ በደል አስተናግዷል።

የግፍ ድርጊቱ መጀመሪያ የሆነው ጥቅምት 24 በዛን ምሽት ስለተፈጸመው ሁኔታ መስክር ቢባል “በወገኑ ጥቃት የተፈጸበመት የመጀመሪያው የአገር መካላከያ ሠራዊት” ብሎ እንደሚመሰክር አያጠራጥርም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም