ለሀገር የማይሆን ሕይወት ስለማይኖረን ዳግም ለመዝመት ተዘጋጅተናል- የቀድሞ ሰራዊት አባላት - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገር የማይሆን ሕይወት ስለማይኖረን ዳግም ለመዝመት ተዘጋጅተናል- የቀድሞ ሰራዊት አባላት
እንጅባራ ጥቅምት 23/2014(ኢዜአ) ለሀገር የማይሆን ሕይወት ስለማይኖረን የክተት ጥሪውን ተቀብለን ዳግም ለመዝመት ተዘጋጅተናል ሲሉ በእንጅባራ ከተማ የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አባልት አስታወቁ።
የእንጅባራ ከተማ ነዋሪ ወታደር አቡኑ አለነ በ1992 በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ቤታቸው የተመለሱ የቀድሞ መከላከያ ሠራዊት አባል ናቸው።
ላለፉት 27 አመታት ሀገር ሲዘርፍ የኖረው የህወሀት ቡድን ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር ሀገር ለማፍረስ ተነሳስቶ በመከላከያ ሰራዊት ላይ በፈጸመው ጥቃት ቁጭት የፈጠረባቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ቡድኑ አሁን ላይ እብሪቱ ተባብሶ ጦርነት በመክፈት ንጹሀንን በመጨፍጨፍ፣ ንብረት በማውደምና በመዝረፍ እየፈጸመ ያለው ተግባር ይባስ ያስቆጣቸው መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት ያቀረበውን ጥሪ በመቀበል ወራሪውን ቡድን ለመፋለም ወደ ግንባር ለመዝመት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል ።
"ዱሮም አካሌን ሰጥቻለሁ፤ አሁንም ለሀገር የማይሆን ሕይወት ስለሌለኝ በጀግንነት ወኔ የጠላትን ቅስም ለመስበር ተዘጋጅቻለሁ" ብለዋል።
ሌላው የቀድሞ ሠራዊት አባልና የከተማው ነዋሪ የመቶ አለቃ አሳየ ቸኮል ወራሪው እየፈጸመ ያለውን ግድያ፣ አስገድዶ መድፈርና ዘረፋን የምናስቆመው ሁላችንም በቁጭት ተነሳስተን መስዋእትነት በመክፈል ነው" ብለዋል።
'ሀገርን ለማፍረስ የተነሳውን ወራሪ ሀይል ለመመከት የህይወት መስዋእትነት ለመክፈል የክተት ጥሪውን ተቀብለው ዳግም ለመዝመት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል ።
''ሐብታችን ሲዘረፍ፣ ቤተ-ዕምነቶች ሲቃጠሉ፣ ሴቶችና ህጻናት ሲደፈሩ ከማየት ሁላችንም እስከ ግንባር በመዝመት ወራሪውን በመደምሰስ ሀላፊነታችንን መወጣት አለብን" ብለዋል።
"ጦርነቱን እስከ ግንባር ለመምራት ዝግጁ ነኝ'' በማለትም ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅር ገልጸዋል።