በአዲስ አበባ የግል የጦር መሳሪያ የታጠቁ ሰዎች ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት የማስመዝገብ ግደታ አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ የግል የጦር መሳሪያ የታጠቁ ሰዎች ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት የማስመዝገብ ግደታ አለባቸው
አዲስ አበባ ጥቅምት 23/2014(ኢዜአ) በአዲስ አበባ የግል የጦር መሳሪያ የታጠቁ ሰዎች ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት የማስመዝገብ ግዴታ እንዳለባቸው የመዲናዋ የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ አሳሰበ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቀነዓ ያደታ በወቅታዊ የፀጥታ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በአዲስ አበባ የተመዘገበም ሆነ ያልተመዘገበ የግል የጦር መሳሪያ የታጠቁ ግለሰቦች ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት የማስመዝገብ ግዴታ አለባቸው ብለዋል።
በመዲናዋ በህዝብ ዘንድ ውዥንብር ለመፍጠር የሚሞክሩ አካላት በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ቀነዓ ከፖሊስ፣ ከመከላከያ፣ የፀጥታ አካላትን ጨምሮ በአዲስ አበባ ዙሪያ ካሉ የሰላምና የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባ የሚኖር ማንኛውም ግለሰብ በእጁ የሚገኙ መሳሪያዎችን "ከዚህ ቀደም ያስመዘገበም ሆነ ያላስመዘገበ ዛሬን ጨምሮ በሁለት ቀን ውስጥ በአቅራቢያው በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ የማስመዝገብ ግደታ አለበት ነው ያሉት።
የጦር መሳሪያው ተመዝግቦ ሕጋዊነቱ ከተረጋገጠ በኋላም የመሳሪያው ባለቤቶች ያራሳቸውንና የአካባቢያቸውን ፀጥታ መጠበቂያ እንዲያውሉት መንግስት አቅጣጫ ማስቀመጡን ጠቁመዋል።
የመሳሪያው ባለቤቶች አካባቢያቸውን መጠበቅና ለጥበቃ መሰማራት የማይችሉ ከሆነ ደግሞ ለቅርብ ሰው ወይም ለመንግሥት በአደራ ሰጥተው አገልግሎት እንዲሰጥ እንደሚያደርጉም አንስተዋል።
የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከመንደር እስከ ቀጣና ተደራጅተው አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ አሰራር መፈጠሩን ጠቅሰው፤ በአደረጃጀታቸው ከፀጥታ ተቋማት ጋር በመናበብ በየአካባቢው የፀጥታ ቁጥጥርና ጥበቃ ያደርጋሉ ብለዋል።
የአዲስ አበባን ሰላም ለማስከበር በየተለያዩ ቤቶችና የንግድ ቦታዎች ላይ የፍተሻ ስራዎች የሚካሔዱ በመሆኑ ህብረተሰቡም ለዚሁ ስኬት ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የቤት አከራዮች፣ ሆቴሎችና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎት ሲሰጡ የግለሰቦችን ማንነት የሚገልጽ ትክክለኛ መታወቂያ መያዛቸውን መጠየቅ አለባቸው ብለዋል ዶክተር ቀነዓ።
መንግስት የጦር መሳሪያ ያስመዘገቡ ሰዎችን ትጥቅ የመውሰድ አላማ እንደሌለው ጠቅሰው የወቅቱን አጋጣሚ በመጠቀም ወንጀል ሊፈፅሙ የሚችሉ አካላትን ለመቆጣጠር መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም በተሰጠው ሁለቱ ቀናት ውስጥ ሳያስመዘግቡ የቀሩ የግል ጦር መሳሪያ የታጠቁ ግለሰቦች ከተገኙ እርምጃ ይወሰዳል ነው ያሉት።
የግልና የመንግስት ጥበቃ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ አካላት ከመንግስት የፀጥታ ኃይል ጋር በተናበበ መልኩ እንዲሰሩም አደራ ብለዋል።
መላው ነዋሪ በብሎክና በመንደር ተደራጅቶ የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት ከፀጥታ ሀይሉ ጋር በቅንጅት መጠበቅ፣ መቆጣጠር እንዲሁም የፀጥታ ሃይሎች፣ የህብረተሰብ ፖሊስና የደንብ ማስከበር አደረጃጀቶች ከመደበኛው የፀጥታ ሃይል ጋር ተቀናጅተው ይሰራሉ ብለዋል።
በመዲናዋ ውዥንብር ለመፍጠር የሚሰሩ አካላት ላይ እርምጃ የሚወሰድ ሲሆን ነዋሪውም ለሰላምና የፀጥታ ስራዎች እያደረገ ያለውን ድጋፍ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
የአዲስ አበባ የፀጥታ ተቋማት ከኦሮሚያ ልዩ ዞን የፀጥታ ሃይሎች ጋር በቅንጅት ተናበው እየሰሩ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ቀነዓ ህዝቡም እያደረገ ያለውን ድጋፍና እገዛ አድንቀው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።