ቀጥታ፡

የአሸባሪዎችን የጭካኔ ተግባር ማስቆም የሚቻው በአንድነት በመቆም ነው - ነዋሪዎች

ግምቢ ጥቅምት 23/2014/ኢዜአ/ የአሸባሪዎችን የጭካኔ ተግባር ማስቆም የሚቻለው በአንድነት በመቆም ነው ሲሉ በምአራብ ወለጋ ዞን የቦጂ ቢርመጂ ወረዳ ነዋሪዎች ገለፁ።

የወረዳው ነዋሪዎች በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ህዝባዊ ውይይት አካሄደዋል።

የከተማው ነዋሪዎች በውይይቱ ወቅት እንዳሉት አሸባሪው ሕወሓት ባለፉት 27 ዓመታት ዘርፎ ባከማቸው የሀገር ሀብት በመታገዝ ኢትዮጵያን ለማፍረስ በመነሳት በንፁሃን ላይ ግፍ እየፈፀመ ይገኛል።

የአሸባሪውን የጭካኔ ተግባር ማስቆም የሚቻው በአንድነት በመነሳት ከመንግስት ጎን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ መሆኑን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

አባሪው ሸኔም በቤጊና ቆንዳላ ወረዳዎች ውስጥ በመንቀሳቀስ የተለያዩ ጥፋቶችን እያደረሰ መሆኑን ጠቁመዋል ።

"አሸባሪ ቡድኖቹን ለማስወገድ በመንግስት እየተወሰደ ያለው እርምጃ ከግብ እንዲደርስ የሚፈለግባቸውን ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ለአገር ሉዓላዊነት መከበር እስከ ግንባር ድረስ በመዝመት አሸባሪዎችን እስከ መጨረሻው ድረስ በመፋለም የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የቦጂ ድርመጂ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ጨነቀ ቡልቻ ባደረጉት ንግግር የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር በመሆን ባደረገው መራራ ትግል ከህወሀት የጭቆና አገዛዝ ተላቆ የመብቱ ተጠቃሚ መሆኑን አመልክተዋል።

"የኢትዮጵያ ህዝብ የተጎናጸፈውን መብት ለመንጠቅ ከውስጥና ከውጭ የተቃጣውን የሽብር ጥቃት ከፀጥታ አካላት ጎን በመቆም የወረዳችንና የአገራችንን ሰላም መጠበቅ አለብን" ብለዋል።

በብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የወረዳው ሃላፊ አቶ ደበላ ተክሉ በበኩላቸው  "ሰላም ከሌለ ሀገር ልትለማ ስለማትችል ከአካባቢያችን ጀምረን ለሰላም መከበር ቅድሚያ ሰጥተን መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል" ብለዋል።

"ህብረተሰቡ ከቤቱ በመጀመር ለአካባቢውና ለሀገር ሰላም መረጋገጥ ዘብ መቆም  አለበት " ሲሉ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም