ቀጥታ፡

የሲዳማ ክልል ህዝብ ለህልውና ዘመቻው ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እንዲዘጋጅ ጥሪ አቀረበ

ሀዋሳ፤ጥቅምት 23/2014 (ኢዜአ) የሲዳማ ክልል ህዝብ ለህልውና ዘመቻው ሁሉን አቀፍ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እንዲዘጋጅ የክልሉ ርዕሰ መስታዳደር ደስታ ሌዳሞ ጥሪ አቀረቡ።
ርዕሰ መስተዳደሩ ዛሬ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

ርዕሰ መስታዳደሩ በመግለጫቸው አሸባሪው ህወሓት በሥልጣን በቆየባቸው አመታት ከፋፋይና የግፍ አገዛዝ ሲያራምድ መቆየቱን አስታውሰዋል።

መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ባደረገው ትግል የቡድኑን ጨቋኝ አገዛዝ ከትከሻው ላይ ማውረድ መቻሉን አመልክተዋል።

ቡድኑ ተቆጣጥሮት ከነበረው የሥልጣን እርከን ዞር ቢልም መቀሌ መሽጎ ከቆየ በኋላ ዳግም ወደ ሥልጣን በመምጣት የተለመደ ጭቆናና ዝርፊያውን ለማስቀጠል አልሞ መንቀሳቀሱን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን በማፍረስ ለርሱና ተልዕኮ ለሚሰጡት የውጭ ኃይሎች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ጦርነት መክፈቱን ጠቅሰዋል።

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የሽብር ቡድኑ በውጭ ኃይሎች ጭምር በመታገዝ በከፈተው የወረራ ተግባር በዜጎችና በሀገር ሀብት ላይ መጠነ ሰፊ ውድመት እያስከተለ በመሆኑ ሰፊ ህዝባዊ ንቅናቄና ሀብት ማንቀሳቀስ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ገልፀዋል።

በመሆኑም የክልሉ መንግስት አሸባሪው ህወሓት ግብዐተ መሬቱ እስከፈፀም ድረስ ለሀገር ህልውና ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሰራ አስገንዝበዋል።

መላው የክልሉ ህዝብ በግንባር ለሚዋደቀው ሰራዊት ደጀን በመሆን ብሎም እድሜና ጤንነቱ የሚፈቅድ ሁሉ በግንባር በመሰለፍ ለህልውና ዘመቻው ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ እንዲሆን ርዕሰ መስተዳደሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በተለይ የሲዳማ ወጣት በህወሓት አገዛዝ ዘመን የመብት ጥያቄዎችን በማንሳቱ ብቻ ሲታፈንና ህይወቱን ሲገብር የቆየ መሆኑን ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ ወጣቱ ኃይልና ከዚህ በፊት በውትድርና ያገለገሉ የክልሉ ነዋሪዎች  የጠላትን ኃይል ባለበት ለመቅበር ወደ ግንባር መዝመት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በግንባር የህይወት መስዋዕትነት እየከፈሉ ለሚገኙት ለአገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላት ደጀን ለመሆንና በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ እንዲቻል ሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ በሚንቀሳቀስበት ወቅት ሁሉም አካል ካለው ላይ በማካፈል ምላሽ እንዲሰጥ መልክታቸውን አስተላልፈዋል።

የክልሉ ሠላምና ፀጥታ አስተማማኝ ሆኖ እንዲቀጥል ህዝቡ የውስጥ ሠላሙን ሊጠብቅ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ህብረተሰቡ ፀጉረ-ልውጦችንና ለጸጥታ ስጋት የሆኑ እንቅስቃሴዎችን በሚመለከትበት ወቅት ለፀጥታ አካላት ከመጠቆም ባለፈ ተባብሮ በመስራት ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያዊያን ኃይል በአንድነት ከተጋመደ ትልቅ አቅም እንደሚሆን የተናገሩት ርዕሰ መስታዳደሩ ''ተባብረን ከሰራን የድሉ ባለቤቶች እኛ እንሆናለን''  ሲሉ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም