ዳያስፖራው ባለበት ሆኖ አገራዊ ድጋፎችን የሚያደርግበት "አይዞን" የተሰኘ መተግበሪያ ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራው ባለበት ሆኖ አገራዊ ድጋፎችን የሚያደርግበት "አይዞን" የተሰኘ መተግበሪያ ይፋ ሆነ
ጥቅምት 23/2014 የዳያስፖራው ማኅበረሰብ ባለበት ቦታ ሆኖ አገራዊ ድጋፎችን የሚያደርግበት "አይዞን" የተሰኘ መተግበሪያ ዛሬ ይፋ ሆኗል።
ቻፓ ፋይናንሺያል ቴክኖሎጂ አክሲዮን ማኅበር ያበለፀገው መተግበሪያው አገልግሎቱን የሚሰጠው ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጄንሲና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመተባበር ነው።
ለዚህም ሶስቱ ተቋማት ዛሬ የስምምነት ሰነድ በመፈራረም መተግበሪያውን ይፋ አድርገዋል።
መተግበሪያው ዳያስፖራው ባለበት ቦታ ሆኖ አገሩንና ወገኑን የሚረዳበትን ምቹ ሁኔታ የያዘ፣ ግልፅነትና ተዓማኒነትም የሚያሰፍን እንደሆነ አብራርተዋል።
ባለፉት 15 ወራት በውጭ አገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን የተናገሩት ዶክተር መሃመድ አዲሱ መተግበሪያ የዳያስፖራውን ተሳትፎ እንደሚያሳድገው ገልጸዋል።
ቀደም ሲል ዳያስፖራው በአገሩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ለመሳተፍ የተለያዩ የሂሳብ ቁጥሮችን መክፈት ያስፈልግ እንደነበረ አስታውሰዋል።
ዳያስፖራው አገሩን ማገዝ ሲፈልግ ገንዘቡን ለመላክ የተለያዩ ቢሮክራሲዎችን ማለፍና ተጨማሪ የመላኪያ ወጪና ገንዘብ ያባክን እንደነበረም ጠቅሰዋል።
አዲሱ "አይዞን" መተግበሪያ ቋሚና ዘላቂ ሆኖ በስሩ የተለያየ ዓላማ ያላቸው የድጋፍ አይነቶችን የያዘ ከመሆኑ ባሻገር ማንኛውም ሰው ባለበት ሆኖ በሞባይሉ የተቻለውን ያህል አስተዋፅኦ የሚያደርግበት ነው ብለዋል።
ለሕዳሴ ግድብ እና ለተፈናቃዮች ማቋቋሚያ የሚውሉ የድጋፍ አይነቶች በመተግበሪያው ከተካተቱ ውስጥ ተጠቃሽ ሲሆኑ የሚገኘው ገንዘብ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ለተፈለገው ዓላማ ይከፋፈላል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ባንኩ ለዚሁ ዓላማ የሚውል የአሰራር ስርዓት መዘርጋቱን ገልጸዋል።
ባንኩ የሚሰበስበው ገንዘብ ለሚፈለገው ዓላማ በትክክል መዋሉን የማረጋገጥ ሃላፊነቱን ይወጣል ሲሉም ተናግረዋል።