ክልሉ ሀገርን ለማዳን የሚደረገውን ማንኛውም ዓይነት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ክልሉ ሀገርን ለማዳን የሚደረገውን ማንኛውም ዓይነት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነው
ጋምቤላ፤ ጥቅምት 23/2014 (ኢዜአ) የጋምቤላ ክልላዊ መንግስት ሀገርን ለማዳን የሚደረገውን ማንኛውንም ዓይነት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ።
የክልሉ መንግስት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ዛሬ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፤ የጥፋት ቡድኑ ጥቅምት 24/ 2013 ዓ.ም በችግሩ ጊዜ ከጎኑ ባልተለየው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ በክህደት ካጠቃ በኋላ በኢትዮጵያውያን ላይ ጥቃት ሲፈጽም ቆይቷል።
ህዝብን ለማጥፋት አስቦና አቅዶ የተነሳውን ኃይል ማሸነፍ የሚቻለው እንደ ህዝብ አንድ ሆኖ በመቆምና በመመከት ብቻ እንደሆነ የክልሉ መንግስት በጽኑ ያምናል ብሏል።
ጠላት በግንባር እየደረሰበት ያለውን ሽንፈት በሀሰት ፕሮፖጋንዳ ለማካካስ እያደረገ ያለውን ጥረት ሁሉም ቀድሞ መረዳት እንዳለበት ነው በመግለጫው ያመለከተው።
አሸባሪው ቡድን ቀድሞ የሚያሰራጨው ሀሰተኛ ወሬ ለወገን ጦር ደጀን የሆነውን ህዝብ ለማደናገር የሚጠቀምበት ስልት መሆኑን በውል መረዳት ይገባል ነው ያለው ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ኢትዮጵያን በአንድነት ከጥቃት ለመከላከል ያቀረቡትን ጥሪ የጋምቤላ ክልል ህዝብና መንግስት በሙሉ ልቡ እንደሚቀበልም አስታውቋል።
ክልሉ ሀገርን ለማዳን የሚደረገውን ማንኛውም ዓይነት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን በመግለጫው አስታውቋል።
የህዝብና ሀገር ጠላት የሆነውን አሸባሪ ህወሓት ግብዓተ-መሬት ለማፋጠን የክልሉ መንግስትና ህዝብ የጀመሩትን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አጠናክረው ይቀጥላሉም ብሏል።
የመግለጫው ሙሉ ቃል ከዚህ እንደሚከተለው ነው
ከጋምቤላ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ ።
የህወሓት ጁንታ ቡድን የዛሬ ዓመት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ከ20 ዓመታት በላይ ሲጠብቀውና በችግሩ ጊዜ ከጎኑ በማይለየው የሰሜን እዝ የመከላከያ ሃይላችን ላይ ታሪክ የማይረሳው ክህደት ከፈጸመ በኋላ በኢትዮጵያውያን ላይ ሁሉንም አይነት ጥቃት ሲፈጽም ቆይቷል።
ህዝብን እንደ ህዝብ ለማጥፋት አስቦና አቅዶ የተነሳን ሀይል ማሸነፍ የሚቻለው እንደ ህዝብ አንድ ሆኖ በመቆምና በመመከት ብቻ እንደሆነ በጽኑ እናምናለን፡፡ ጠላት ከመሳሪያው በላይ በሚለቃቸው ፕሮፓጋንዳዎች ካሸበረን አንድ ሆነን መቆም ስለማንችል ህልውናችንን ለማስቀጠል እንቅፋት ይፈጥራል፡፡
በመሆኑም ጠላት በግንባር እየደረሰበት ያለውን ሽንፈት በሀሰት ፕሮፖጋንዳ ለማካካስና የጦሩን ስነ ልቦና ለመገንባት እንዲሁም ለወገን ጦር ደጀን የሆነውን ህዝብ ለማደናገር የሚጠቀምበት የውሸት ታክቲክ መሆኑን በውል በመረዳት ወቅቱን የሚመጥን ስነ-ልቦና መገንባት ለነገ የሚባል አይደለም።
ትላንትና ከኋላው የተወጋውና ታሪክ ሊረሳው የማይችል መራራ በደል የደረሰበት ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን በጀመረው አዲስ የማሸነፍ ተጋድሎው እና መቼም በማንም ሊቆም በማይችለው ሀገርን የማሻገር ሩቅ ጉዞው ይህንን የጥፋት ቡድን አይቀጡ ቅጣት እንደሚቀጣው ምንም ጥርጥር የለንም፡፡
ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ ለይቅርታ የተዘረጉ እጆችን ትቶ- በእብሪት እና ትምክህቱ ጸንቶ- እኩልነትን በመጸየፍ የበላይነትን ብቻ በመፈለግ የሀገር ክንድ በሆነው መከላከያችን ላይ የፈጸመውን አረመኔያዊ ድርጊት የጋምቤላ ህዝብ እና የክልላችን መንግስት ሁሌም በቁጭት ያስታውሱታል፡፡
ውጊያችን ከህወሓት የጥፋት ቡድን ጋር ብቻ ሳይሆን በዚህ እኩይ ቡድን ኢትዮጵያን የማጥፋት እኩይ ፍላጎት ውስጥ ከተሰገሰጉ የውጭ እና የውስጥ የጥፋት ሀይሎች ጋርም ጭምር እንደሆነ ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡
በመሆኑም ወገናችን የሆንከው የትግራይ ህዝብ ከሠላም ወዳዱ ህዝባችን ጎን በመቆም በልጆችህ ህይወት ቁማር የሚጫወት እና ለአንድነታችን፣ ለሠላም፣ ሉዓላዊነት ነቀርሳ የሆነውን ይህን የጥፋት ቡድን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ እየተደረገ ባለው ርብርብ ከጎናችን እንድትሆን ወንድማዊ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
በሌላ በኩል የልማታችን ፀር የሆነውን የጁንታውን ቡድን በአጭር ጊዜ ውስጥ ደምስሰን ፊታችንን ወደ ልማት ተግባሮቻችን ለመመለስ የክልላችን ሕዝቦች ከሀገር መከላከያ ጎን እንዲቆም የክልሉ መንግስት ጥሪውን ያስተላልፋል።
የክልላችን መንግስትና መላው የክልላችን ነዋሪዎች በማስተባበር ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን አሸባሪውን ቡድን ለመደምሰስ እየወሰደ ያለውን እርምጃ በሰው ኃይል፣ በአይነት፣ በገንዘብና በሞራል እየደገፈ የቆየ ቢሆንም ካለው ወቅታዊ አሳሳቢ የህልውና ጉዳይ ይህንን የህዝባችን ጠላት የሆነውን የጥፋት ቡድን ግብዓተ- መሬቱን ለማፋጠን የጀመሩትን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አጠናክረው ይቀጥላሉ።
ኢትዮጵያ በዘመናት መካከል የገጠሟትን የህልውና አደጋዎች በሙሉ የቀለበሰችው በህዝቦቿ ጠንካራ አንድነትና የተባበረ ክንድ ነው። በዚህ ዘመን ኢትዮጵያን ካልዘረፍኳትና እንደወትሮው ረግጬ ካልገዛኋት ትፍረስ በሚል ስግብግብ ፍላጎት ክህደት የፈጸመብንና ጦርነት የከፈተብንን የህወሓትን ወራሪ ቡድን የምንሰብረውና የምንቀብረውም ከታሪካችን በወረስነው በዚሁ የጀግንነትና የአንድነት መንፈስ ብቻ ነው።
በመሆኑም ትግላችን ዋጋ ማስከፈሉ ባይቀርም የመጨረሻዋን ድል የምንቀዳጀው እኛ መሆናችንን ግን በፍጹም አንጠራጠርም፡፡ በዘመን መስመር ላይ በፍጹም ፍጥነት አሸባሪው ህወሓት ያጠፋቸውን ብዙ ነገሮች በብዙ ትጋት- ቁርጠኝነት- ፍጥነት- መሰጠት እና አንድነት ለማስተካከል የሚደረገው ትግል የራሱን ተፈጥሯዊ ጊዜ መውሰዱ አይቀርም፡፡
የክልላችን ፀጥታ አካላትና ወጣቶች ክልላችን ጋምቤላ ድንበር ላይ የሚገኝ በመሆኑ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በውስጥ የጋምቤላ ነፃነት ግንባር፣ የሸኔ ታጣቂዎችና የጁንታውን ዓላማ የሚያራግቡ ጥቂት ፀረ-ሠላም ኃይሎች የሚንሳቀሱበት በመሆኑ፤ በውጪ ደግሞ የዘመናት ታሪካዊ ጠላቶቻችን በቅርበት የሚገኙበት በመሆኑ በንቃት አካባቢያችንን እንድትጠብቁ እና የጀመርነውን ሁሉን አቀፍ የልማት እንቅስቃሴ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የጋራ ሰላም ለማስከበር ለሚደረገው ጥረት የህብረተሰቡን ፀጥታና ደህንነት በመጠበቅ ሃገራዊ ግዴታችሁን እንድትወጡ የክልሉ መንግስት ያሳስባል።
ይህም ሆኖ ግን ወራሪው ሀይል የከፈተብን መጠነ ሰፊ ወረራም ሆነ ሌሎች እኩይ ፕሮጀክቶቹ በህዝባችን አይተኬ ሚና እና ለዚህ በጀገኑ የሀገራችን የቁርጥ ቀን ልጆች ርብርብ ሁሉም በድል ይጠናቀቃል፡፡
የክልሉ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የተደቀነውን የህልውና አደጋ በአጭር ጊዜ ለመቀልበስ ከህዝቡና ከሁሉም የኢትዮጵያ ወዳጆች ጋር እጅና ጓንት ሆኖ በቁጭትና በጥድፊያ መንፈስ እንደሚሰራም በዚሁ አጋጣሚ ይገልጻል።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ኢትዮጵያን በአንድነት ከጥቃት ለመከላከል ያቀረቡትን ጥሪ የጋምቤላ ክልል ህዝብና መንግስት በሙሉ ልቡ የሚቀበል መሆኑን እየገለጽን ሀገርን ለማዳን የሚደረገውን ማንኛውም አይነት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናችንን በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡
በዚህ አጋጣሚ ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን፣ ሌሎች የጸጥታ አካላት እና ደጀን የሆነው የሀገራችን ህዝብ ሀገርን ከአሸባሪው የህወሓት ቡድን ለመጠበቅ እያደረጉ ላሉት ተጋድሎና እየከፈሉት ላለው ወድ መስዋዕትነት ያለንን ልባዊ አክብሮት እንገልፃለን፡፡
ጠላት የመጨረሻ እድሉን አሟጦ እየተጠቀመ ያለበት ሰዓት በመሆኑ የጦርነትን ባህሪ መረዳትና በሀሰት ከሚራገቡ የማህበራዊ ሚዲያ ወሬዎች ራሳችንን በመጠበቅ ሁሉም እንደ አቅሙ በህልውናው ላይ የመጣን አደጋ ለመቀልበስ ራሱን ማዘጋጀትና የመኖር ዋስትናውን በራሱ ለማረጋገጥ ቆርጦ መነሳት ይኖርበታል።
ኢትዮጵያ እያሸነፈች ትቀጥላለች!
የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት
ጥቅምት 23/2014ዓ.ም