ምክር ቤቱ ሀገርን ለማዳን በሚደረገው ፍልሚያ ከሁሉ ተግባር ቅድሚያ ተሰጥቶ ርብርብ እንዲደረግ ጥሪ አቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ ሀገርን ለማዳን በሚደረገው ፍልሚያ ከሁሉ ተግባር ቅድሚያ ተሰጥቶ ርብርብ እንዲደረግ ጥሪ አቀረበ
ሀዋሳ ፤ ጥቅምት 23/2014 (ኢዜአ) የደቡብ ክልል ህዝቦችና አመራሮች ሀገርን ለማዳን በሚደረገው ፍልሚያ ከሁሉ ተግባር ቅድሚያ ሰጥተው በሙሉ ሃይል እንዲረባረቡ የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ።
ምክር ቤቱ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ፤ ወጣቶች ጀግናው የመከላከያ ሃይሉን እንዲቀላቀሉና መላው ህዝብ ደግሞ ጠላትን ለመመከት ሁሉን አቀፍ ድጋፉን በማጠናከር አካባቢውን ከሰርጎ ገቦች እንዲጠብቁ ውሳኔ መተላለፉን አስታውቋል።
የክልላችን ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች የኢትዮጵያ ጠላት የሆነውን አሸባሪው የህወሃት ቡድን ሴራን በማክሸፍ የሀገራችንን ህልውና ለማረጋገጥ እንደቀድሞ ሁሉ አሁንም ግንባር ቀደም ተሰላፊ ይሆናሉ ብሏል በመግለጫው ።
በተንኮል ተወልዶ በሴራ ፖለቲካ የኖረው እራሱን የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ብሎ የሰየመው ዘራፊና አጥፊ ቡድን ለ27 ዓመታት በክልሉ ህዝቦች ብሎም በመላው ኢትዮጵያዊያን ላይ ከፍተኛ በደልና ክህደት መፈጸሙን ተወስቷል።
በሽብር ቡድኑ እኩይ ተግባር የተማረረው መላው ኢትዮጵያዊያን መራር ትግል ተወግዶ በህዝቦች ፍላጎት የመጣው የለውጥ ሂደታችንን ለመቀልበስ ያልሸረበው ሴራ አልነበረም ብሏል ምክር ቤቱ በመግለጫው።
ለአብነት በክልሉ በዚህ የሽብር ቡድን አቀናባሪነት በተከሰቱ ግጭቶች የበርካታ ዜጎቻችን ህይወትና ንብረት ውድመት ደርሷል፣ ተፈናቅለዋል ሲል ጠቅሷል።
ይህ በቀቢጸ ተስፋ የተሞላ ቡድን ሀገር የማፍረስ እኩይ ተግባሩን አጠናክሮ በመቀጠል በአማራና አፋር ክልል ህዝቦች የማያቋርጥ የህልውና ስጋት መደቀኑን ተመልክቷል።
ይህ የጥፋት ቡድን ትውልድን ሲያመክን የኖረ፣ ከውጭ ጠላት በላይ የኢትዮጵያን ክብር ያዋረደ ሰው በላ ስርዓት እስከወዲያኛው ታሪክ ሆኖ እንዲቀር የጠነከረ አንድነት እንደሚያስፈልግ ምክር ቤቱ ገልጿል።
የሽብር ቡድኑን መደምሰስ ደግሞ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው ያለው የመስተዳድር ምክር ቤቱ መግለጫ፤ መላው የክልሉ ህዝብ ቡድኑን በመገርሰስ ረገድ ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል።
ጀግኖች አባቶቻችን ከጠላት ጠብቀው ያቆዩትን ሀገር ከነክብሯ ለማሻገር ያለው አማራጭ ሁሉ በመጠቀም ቡድኑን ለመጨረሻ ጊዜ መደምሰስ ይጠበቅብናል ብሏል ምክር ቤቱ።
ሀገር የመበተን ዓላማውን ለማሳካት በዜጎች ላይ እያደረሰ ያለው ግፍና የሰቆቃ ጊዜያት እንዲያበቃ ለሀገራችን ህልውና በቁጭት መታገል አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑ ተመላክቷል።
ትግሉ ኢትዮጵያን የመበተን እኩይ ፍላጎት መሰረት በማድረግ ከአጥፊ ቡድን ጋር ያበሩ የውጭ እና የውስጥ የጥፋት ተባባሪዎችም ጭምር እንደሆነ ጠንቅቀን እናውቃለን ብሏል መግለጫው።
መላው የክልሉ ህዝቦች የሽብር ቡድኑ ተላላኪዎችንና ሰርጎ ገቦችን አካባቢውን ነቅቶ በመጠበቅ በግንባር እየተዋደቀ ላለው የጸጥታ ሃይል የሚደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍና ደጀንነት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠይቋል።
ህልሙን በተግባር ለማሳካት ያልቻለው ቡድኑ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ እየነዛ መሆኑን በመረዳት የጠላት ሃይል ግብአተ መሬት ለመፈጸም መላው ህዝብ በአንድነት እንዲንቀሳቀስ ብሏል ምክር ቤቱ በመግለጫው።
የክልሉ ወጣቶችም ጀግናው የመከላከያ ሰራዊትን እንዲቀላቀሉ፤ ሌላው የህብረተሰብ ክፍልም አካባቢውን ተደራጅቶ በንቃት እንዲጠብቅና በየደረጃው ያለው አመራርም ምልዓተ ህዝቡን በማስተባበር በግንባር ቀድምትነት እንዲንቀሳቀስ ምክር ቤቱ መወሰኑን በመግለጫው አስታውቋል፡፡
ጠብቅ፣ ዝመት፣ ደግፍ
_ አካባቢህን ጠብቅ
_ ወደ ግንባር ዝመት
_ መከላከያን ደግፍ