ህዝቡ የመንግስትን የክተት ጥሪ ተቀብሎ የህልውና ዘመቻውን ፈጥኖ ሊቀላቀል ይገባል

ባህር ዳር ፤ ጥቅምት 22/2014 (ኢዜአ) ወራሪውንና አሸባሪውን ህወሓት ለመመከትና ለመደምሰስ ህዝቡ የመንግስትን የክተት ጥሪ በመቀበል ዘመቻውን ፈጥኖ እንዲቀላቀል የባህር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ ጥሪ አቀረቡ።

የክተት ጥሪውን ተከትሎ የግልና የመንግስት ታጣቂዎች የህልውና ዘመቻውን ለመቀላቀል እየተመዘገቡ መሆኑንም ከንቲባው ጠቁመዋል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በወቅታዊ ጉዳይ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፣ በህልውና ዘመቻው የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሺያ እና ፋኖ ጠላትን በግንባር እየተፋለሙ ይገኛል።

አሸባሪውና ወራሪው ኃይል ጦርነቱን ህዝባዊ ማድረጉን ተከትሎ በርካታ የአማራ ክልል አካባቢዎችን በመውረር ሃብትና ንብረት እየዘረፈ፣ የዜጎችንም ህይወት እየቀጠፈ መሆኑን ገልፀዋል።

ይህንን ወራሪ ቡድን ለመደምሰስ የፀጥታ ሃይሉ በተቀናጀ አግባብ ግንባር ላይ እየተፋለመ መሆኑን ጠቅሰው፣ "ለፀጥታ ሃይሉ ህዝባዊ ማዕበል በመፍጠር እገዛ ማድረግ ይገባል" ብለዋል።

ለዚህም የክልሉ መንግስት የክተት ጥሪ ማቅረቡን ተከትሎ የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመፍጠር አፋጣኝ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።

ዶክተር ድረስ እንዳሉት የክተት ጥሪውን ተከትሎ የግልና የመንግስት ታጣቂዎች የህልውና ዘመቻውን ለመቀላቀል በገጠር ቀበሌዎችና በየክፍለ ከተማው እየተመዘገቡ ይገኛሉ።

በተጠባባቂ ኃይልነት ሰልጥነው በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ በርካታ ወጣቶችም በአሁኑ ወቅት ወደ ግንባር ለመዝመት ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ነው የተናገሩት።

ከዚህ ጎን ለጎንም ለመከላከያና ለልዩ ኃይል ስልጠና የሚገቡ ወጣቶች ምልመላና ምዝገባ እስከ ጥቅምት 25 ቀን 2014 ድረስ እንደሚከናወን አመልክተዋል።

"ወራሪውን ኃይል በህዝባዊ ማዕበል በአጭር ጊዜ በመደምሰስና የህልውና ዘመቻውን በማጠናቀቅ ፊታችንን ወደ ልማት ለማዞር ሁሉም የክተት ጥሪውን እንዲቀላቀልም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው" ጥሪ አቅርበዋል።

የክተት ጥሪውን ተቀብሎ ለመዝመት በየአካባቢው እየተመዘገበ ያለውን ኃይል አደራጅቶ ወደ ግንባር ለመዝመትና ለማዋጋት አመራርና ስምሪት መሰጠቱንም ዶክተር ድረስ አብራርተዋል።

በስምሪቱም የሎጀስቲክስ፣ የአካባቢን ሰላም ማስጠበቅና ግንባሩን በበላይነት የሚመራ አደረጃጀት መፍጠር  እንደሚገባ አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል።

አመራሩ የህልውና ዘመቻውን በበላይነት ሆኖ እንደሚመራም ምክትል ከንቲባው አስረድተዋል። 

ከወራት በፊት የባህር ዳር ከተማን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመታወጁና ወጣቱና የፀጥታ ኃይሉ ተቀናጅቶ መስራቱ ውጤት ማስመዝገቡን አስታውሰዋል። 

በአሁኑ ወቅትም እዚህ የሚቀረው ህዝብ በመደራጀት አካባቢውን ከሰርጎ ገቦች ነቅቶ ሊጠብቅ እንደሚገባ ዶክተር ድረስ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም