ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ ብሎ የተነሳውን አሸባሪ ቡድን በግንባር በመፋለም ሃገራችንን እናድናለን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ ብሎ የተነሳውን አሸባሪ ቡድን በግንባር በመፋለም ሃገራችንን እናድናለን
መተማ ፤ ጥቅምት 22/2014 ኢዜአ) ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ ብሎ የተነሳውን አሸባሪ ቡድን ቆሞ በመጠበቅ የታሪክ ተወቃሽ ላለመሆን በግንባር ተሰልፌ እፋለመዋለሁ ትላለች በምዕራብ ጎንደር ዞን የአይከል ከተማ ነዋሪዋ ወጣት ናርዶስ አለሙ።
ወጣቷ መንግስት ያደረገውን የክተት ጥሪ ተቀብላ ለመዝመት ዝግጁ መሆኗን ጠቅሳ፤ ይህንን የሃገርና የህዝብ ጠላት የሆነውን ቡድን ለመደምሰስ በሚደረገው ትግል በግንባር በመሰለፍ ለመፋለም መዘጋጀቷን ገልጻለች።
በዘመናዊ መሳሪያና ወታደር በውጭ ጠላት የተፈጸመውን ጥቃት ባልተደራጀ የሰው ኃይል ማሸነፍ የተቻለው በህዝባዊ አንድነት እንደመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጠላትን ለማስወገድ የሚያደርጉት የህልውና ትግል በድል እንደሚጠናቀቅም ተናግራለች።
በዞኑ ጭልጋ ቁጥር 1 ወረዳ ነዋሪው አቶ ብላታ ጥላሁን በበኩላቸው አሁን ያለው ትውልድ የታሪክ ተወቃሽ እንዳይሆን ሀገሩን ከጥፋትና ከመፍረስ መታደግ ይኖርበታል ብለዋል።
''ኢትዮጵያ ለጥቁሮች መመኪያ ለአፍሪካዊያን ደግሞ ኩራት የሆነችው አባቶቻችን በአንድነት በመቆም በዘመናዊ የጦር መሳሪያና አደረጃጀት የተዋቀረውን ሀያል ሀገር ጣሊያንን በመመከታቸው ነው'' ብለዋል።
ከውጭ ጠላት ጋር በማበር የሀገሪቱን ታሪክ ጥላሸት ለመቀባት የሚጥሩ ሀይሎችን በአንድነት ለመከላከል በሚደረገውን ዘመቻ ላይም የትውልድ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
ሌላው የነባሪ ጭልጋ ወረዳ ነዋሪና የቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት አባል የነበሩት አቶ ደሴ መኮንን እንደተናገሩት ያላቸውን ልምድ በመጠቀም ወደ ግንባር ለመሄድና ዛሬም እንደትናንቱ በደማቸው ታሪክ ለመፃፍ ወስነዋል።
''ሀገሬን እወዳለሁ ማለት በቃላት ብቻ የሚገለጽ አይደለም'' ያሉት ነዋሪው አቅሙና ችሎታው ያለው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ወደ ግንባር በመሄድ ሀገሩን ማዳን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ሀገርን ከወራሪ መታደግና ሉዓላዊነቷን ማስጠበቅ የዜግነት ግዴታ በመሆኑ ለሃገራቸው ክብርና ዝና ሲሉ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
“የህወሃት የሽብር ቡድን ከዚህ በላይ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ላይ ጉዳት እንዲያደርሱ መፍቀድ አይገባም” ያሉት ደግሞ በዞኑ መተማ ወረዳ መቃ ቀበሌ ነዋሪ አቶ እያዩ ተዋበ ናቸው።
''ለሀገር መሞት ክብር ነው'' ያሉት ነዋሪው የክልሉ መንግስት ያቀረበውን የክተት አዋጅ በመቀበል ወደ ወሎም ይሁን ሌላ ግንባር ለመሄድ መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።
ዘመቻው የህልውና በመሆኑ የትኛውም የህብረተሰብ ክፍል የሚችለውን በማድረግ ማሸነፍ ግዴታ የሆነውን ትግል በጋራ በመትመም ሀገርን ማዳን እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል።