ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አንድነትን የሚያዳክሙ አስተሳሰቦችን 'በቃችሁ' ማለት እንደሚገባ አመለከተ

አዲስ አበባ ነሀሴ 13/2010 ህዝበ ሙስሊሙ እስልምና የአንድነትና የሰላም ሃይማኖት መሆኑን በመገንዘብ የሚለያዩና መጤ የሆኑ አስተሳሰቦችን ይበቃል ማለት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተወካይ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ዑመር ኢድሪስ ገለጹ። የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ፕሬዚዳንት ሐጅ መሐመድ ሸሪፍ በበኩላቸው ከዚህ በፊት የአረፋ ክብረ በዓል በየመስጊዱ ይካሄደ እንደነበረ ጠቅሰው የዘንድሮ በዓል ግን አንድነትና ፍቅርን በሚሰብክ መልኩ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይከበራል ሲሉ ገልጸዋል። ሚንበር መልቲ ሚዲያ ፕሮዳክሽን ከኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከተለያዩ የሙስሊም ተወካይ ማህበራትና ከእምነቱ ተከታዮች ጋር በመሆን 1439ኛውን የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል "አንድ ሆነን አንድ እንበል" በሚል መሪ ቃል በአወሊያ ትምህርት ቤት አክብረዋል። በዚህ ጊዜ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተወካይና የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ የኮሚቴ ሰብሳቢ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ዑመር ኢድሪስ እንደገለጹት፤ እስልምና አንድነትን፣ ፍቅርን፣ ሰላምና ከሌሎች ጋር ተከባብሮ መኖርን የሚሰብክ ሃይማኖት ነው። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቅድመ አያቶቻችን፣ በአያቶቻችንና በአባቶቻችን ያልነበረ ለያይና መጤ አስተሳስብ ሃይማኖታችንን ሲጎዳ ቆይቷል። ስልሆነም ህዝበ ሙሲሊሙ እስልምና የአንድነት፣ የሰላም፣ የልማት፣ የመቀራረብ፣ የመከባበር፣ የተቸገሩትን የመርዳትና የማዘን ሃይማኖት መሆኑን አውቆ የአረፋን በዓል አንድነትን የሚጎዱና የሚለያዩ አስተሳሰቦችን ''ይበቃል'' በማለት ማክበር አለበት ብለዋል። በተለይ ዘንድሮ በአገሪቷ እየመጣ ያለው የሰላም፣ የይቅርታና የአንድነት መንፈስ ለህዝበ ሙስሊሙ ወሳኝ መሆኑን በመረዳት ለተግባራዊነቱ በንቃት መሳተፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ የጋራ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ በበኩሉ ነብዩ መሃመድ ኢትዮጵያ የፍትህ፣ የእኩልነትና የመከባበር አገር መሆኗን በመረዳት ተከታዮቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ መላካቸውን አስታውሰዋል። ስለሆነም በኢትዮጵያ ፍትህ፣ እኩልነትና መከባበር እንዲጎለብት እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ የተጀመረው የሰላም፣ የአንድነትና የይቅርታ ዘመን ሙሉ በሙሉ እንዲሳካና እንዳይቀለበስ ህዝበ ሙስሊሙ ከመንግስት ጎን መቆም አለበት ሲሉ አሳስበዋል። የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ፕሬዚዳንት ሐጅ መሐመድ ሸሪፍ ከዚህ በፊት የአረፋ በዓል በየመስጊዱ ይካሄድ እንደነበር ጠቅሰው የዘንድሮ በዓል ግን አንድነትና ፍቅርን በሚሰብክ መልኩ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይከበራል ሲሉ ገልጸዋል። በመሆኑም ህዝበ ሙስሊሙ ከዚህ በፊት ከሚያደርገው ሃይማኖታዊ ግዴታ በተጨማሪ በክብረ በዓሉ ላይ ሁሉም አንድነቱንና ሰላምን በጠበቀ መልኩ በዓሉን እንዲያከብር ጠይቀዋል። የሚንበር መልቲ ሚዲያ ፕሮዳክሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አዩ አደም ክብረ በዓሉን ማዘጋጀት ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት የተጀመረውን የአንድነት፣ የመተጋገዝና የሰላም ጉዞ ከዳር ለማድረስ ነው ብለዋል። በተለይም የዛሬው ክብረ በዓል በአወሊያ ትምህርት ቤት መዘጋጀቱ ህዝበ ሙስሊሙ ለበርካታ ዓመታት የመብት ጥያቄ ሲያነሳበትና ልዩነት የፈጠረበት ጉዳዮች ወደ አንድ ለማምጣት ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳወቅ ነው ሲሉ አስታውቀዋል። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት የእምነት ተከታዮች በምክንያትና በውይይት በመካከላቸው ተፈጥሮ የነበረውን ልዩነት ወደ አንድ ማምጣታቸው ለአገሪቱ አንድነት መጠናከር የበኩሉን አስተዋጾኦ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። በቀጣይም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባህላዊ የግጭት አፈታት ላይ ብቻ ሳይሆን ሰላምንና አንድነትን የሚሰብኩ ሃይማኖታዊ እሴቶች ለማጎልበትን እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም