አውቀውም ይሁን ሳያውቁት ጠላትነት - ኢዜአ አማርኛ
አውቀውም ይሁን ሳያውቁት ጠላትነት
በአርቲስት ደበበ እሸቱ
በአገራችን ኢትዮጵያ ጉዳይ ልንደራደር ፈቃድ የለንም። አገራችንን አሳልፎ ለበላተኛ ማሳለፍ ቀርቶ ማሰብም እንኳን ፈቃድ የለንም። አገራችን ስንል ሕዝቡን ጭምር፣ ሕዝቡ ስንል በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደረውን ነው። ሕዝቡ ስንል ለአገሩ ገደብ የሌለውን የትም፣ መቼም፣ በምንም ሸብረክ የማይለውን ነው።
ሕዝቡ ስንል የአገሩን ገበና አሳልፎ ለክፉ አላሚዎች የማይሰጠውን ነው።አሁን ያለንበት ወቅት ኢትዮጵያን ከሃዲ ልጆቿ ጠላት ሆነው በባእዳን ፍላጎት እየተመሩ ሊያጠፏት እየተንደፋደፉ ያሉበት ነው። "ደደብ ጭንቅላት መብሰሉ ላይቀር የሰው ማገዶ ያስጨርሳል" ከሃዲዎችም መቀበራቸው ላይቀር ጥይት ያስጨርሳሉ። እውነቱ ይህ ነው።
የአገር ክህደት በብዙ መልኩ ይተገበራል። አሁን ማንሳት የምፈልገው ወዳጅ መስሎ ጠላትነት፣ አጋር መስሎ እኩይነት የተጠናወታቸውን ነው።
ጦርነት የተከፈተብን ከሽብርተኞቹ ህወሃቶች ጋር ብቻ ሳይሆን፣ በከሃዲዎቹ አረመኔዎች ከሥልጣን መወገድ ጥቅማቸውና ፍላጎታቸው "በቃ!" ተብሎ በተጨናገፈባቸው አገራት ጭምር ነው።
ባይደን ቀድሞ እንደነበረው፣ አሁንም በኢትዮጵያ ማዘዝ መፍለጥ መቁረጥ ፈልገው ስላልተሳካላቸው የሌሎቹን አገራትም መሪዎች እንዲተባበሩዋቸውና ኢትዮጵያን አሸባሪው ህወሃት ካልገዛት እንዲያፈራርሳት መርዳት አለብን በሚል እሳቤ ለከሃዲዎቹ አሸባሪዎች ደጋፊ ሆነው፣ እኛንም ለልማት፣ ለዴሞክራሲ፣ ለፍትህና እኩልነት ... እውን መሆን በመቃወም እየወጉን ነው።
ቢቢሲ፣ አል-ጀዚራ፣ ሲኤንኤን፣ ሲቢሲ ያልሆነውን ሆነ ብሎ ለማሳመን መተረኩን ተያይዘውታል፣ በተለይም አሶሽዬትድ ፕሬስ የሚባለው የዜና ወኪል ያካበተውን ክብሩን ለአሸባሪው ህወሃት ሲል ባቀረበው የፈጠራ ዜና በዓለም ላይ በመበተኑ፣ ክብርና ሞገሱን ተገፎ ተአማኒነቱም ተንዷል።
ይህንኑ የፈጠራ ወሬ ደሴ በአሸባሪው ተያዘ የሚለውን የቅጥፈት ከአፈ ሰፊውና አለብላቢት ምላሰኛው ግትቻው ረዳ የተቦለከተውን ሳያገናዝቡ በዩቲዩባቸው ላይ ገልብጠው ሊያስከትል የሚችለውን ሕዝባዊ መደናገጥ ግምት ሳይሰጡት ማቅረባቸው በእጅጉ አሳዛኝ ነው።
እነዚህ ባለቲዩቦች እውነታውን በግምባር በጦሩ አውድማ ላይ ሀገር ወገን ብለው ከተሰለፉት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትና ሌሎች ዘጋቢዎች በመውሰድ ፈንታ ለምን የውጭ ዘጋቢዎች በስልክ የተነገራቸውን ማቅረብ መረጡ? ይህ መመለስ ያለበት በነሱው በባለቲዩቦቹ ቢሆንም የሚመለከተው አካል ሊያግዳቸው ይገባል።
ማገድ ስል ይዝጋ ለማለት ሳይሆን ሀይ ይበላቸው ለማለት ነው።
ይህ ነው አውቀውም ይሁን ሳያውቁትም ጠላትነት ማለት።_
ጠብቅ፣ ዝመት ደግፍ
_ አካባቢህን ጠብ
_ ወደ ግንባር ዝመት
_ መከላከያን ደግፍ