ቀጥታ፡

መንግስት የአገር አንድነት ለመሸርሸር ከአሸባሪው ጋር የሚሰሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳሰበ

ጥቅምት 22 /2014 (ኢዜአ) የአገርን አንድነትን ለመሸርሸር ከአሸባሪው ህወሓት ጋር የሚሰሩ አካላት እጃቸውን እንዲሰበስቡ መንግስት ማሳሰቢያ ሰጠ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ የአሸባሪው ህወሓት ኃይል ኮምቦልቻ ከተማ ሰርጎ በመግባት ዛሬ ሌሊት ከ100 በላይ የከተማዋን ወጣቶች አሰልፎ መጨፍጨፉን ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ በማኅበራዊ ሚዲያ ሕዝብ እና መንግሥትን ለመከፋፈልና የአገሪቷን አንድነት ለመሸርሸር  ከአሸባሪው ጋር የሚሰሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

መንግስት በአገር አንድነት የመጡ አካላት ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን የተናገሩት ሚኒስትሩ ይህም ቀጣይነት የሚኖረው ተግባር መሆኑን አክለዋል።

መንግስት እንደተዳከመ አድርገው የሐሰት ፕሮፓጋንዳ መንዛት ተገቢ አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ አሸባሪውን ቡድን መመከት የሚያስችለው ሙሉ ቁመና እንዳለው ነው የተናገሩት።

አሸባሪው ህወሓት በያዛቸው አካባቢዎች የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ደጀን የሆነው ሕዝብ እስከሚደርስላቸው ድረስ ተጋድሏቸውን እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም