ቀጥታ፡

ሠራዊቱ የተሰነዘረበትን ጥቃት በመመከት አገር የማዳን ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ ነው

ጥቅምት 21/2014 (ኢዜአ) የመከላከያ ሠራዊት የተሰነዘረበትን ጥቃት በመመከት አገር የማዳን ተልዕኮውን በብቃት በመወጣት ላይ እንደሚገኝ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ በሰጡት መግለጫ ሠራዊቱ በሁሉም ግንባሮች የተከፈቱበትን ጥቃቶች በብቃት በመመከት ላይ ይገኛል።

አሸባሪው ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ በተሁለደሬ፣ ደላንታ፣ ኩታበር፣ ጭፍራ እና ደሴ ግንባሮች ጥቃት መክፈቱንም ገልጸዋል፡፡

ሠራዊቱ ጥቃቱን በብቃት በመመከት አገር የማዳን ተልዕኮውን በአግበቡ በመፈጸም ይዞታውን በማስፋት ላይ እንደሚገኝም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።

አሸባሪው ቡድን ደጀን ላይ በኢትዮጵያ አየር ሃይል በተወሰደበት እርምጃ ከባድ መሳሪያዎቹ እንደወደሙበት ገልጸዋል፡፡

በዚህም አሸባሪው ቡድን አለኝ የሚውን ሃይል አሰባስቦ ከሠራዊቱና ከልዩ ሃይሎች ከባድ መሳሪያና የቡድን መሳሪያችዎን የማግኘት አጀንዳ ይዞ ቢንቀሳቀስም በሠራዊቱ ተጋድሎ ሃሳቡ መክሸፉን ጠቁመዋል።

ሠራዊቱ አሸባሪውን ሃይል በመጣበት አኳሃን በመመከት በሁሉም ግንባሮች እኩይ ዓላማውን ሳያሳካ ከፍተኛ ኪሳራ እያደረሰበት መሆኑንም አክለዋል፡፡

ትናንትና በደሴ ግንባር ሠራዊቱ ወራሪውን ሃይል በመመከት ላይ እያለ ከተማዋ ውስጥ በነበሩ ሃይሎች ጥቃት እንደተሰነዘረበትም ገልጸዋል፡፡  

ሠራዊቱ አሸባሪው ቡድን ቀድሞ ባስገባቸው ሰርጎ ገቦችና ሲቪል ለብሰው ደሴ በነበሩ ባንዳዎች አማካኝነት ከውስጥ ጥቃት ቢደርስበትም ጥቃቱን መክቶ የማጥቃት እርምጃ በመውሰድ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ዛሬ ሠራዊቱ በታላቅ ተጋድሎና በሙሉ ቁመና አሸባሪው የከፈተበትን ጥቃት በመመከት ላይ እንደሚገኝ አክለዋል።

ሚኒስትሩ ህብረተሰቡ አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ የውስጥ ባንዳዎችን በመከታተል እንዲያጋልጥም አስገንዝበዋል።

የመከላከያ ሠራዊቱን እንቅስቃሴ ለማወክ የተነሱም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አሸባሪው ቡድን ከአማራ እና ከአፋር ክልሎች ሃብትና ንብረቶችን በመዝረፍ ራሱን ለማጠናከር እንቅስቃሴ ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ይህ እኩይ ዓላማው ከግብ እንዳይደርስ ሁሉም ክልሎች ባወጁት የክተት ጥሪ አማካኝነት ኅብረተሰቡ አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡  

መላው የኢትዮጵያ ወጣቶችም ይህን ጥሪ በመቀበል አገራቸውን ለማስከበር እንዲነሱም ጠይቀዋል።

ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብም አሸባሪው ቡድን እየፈጸመ ያለውን ጥቃትና ያደረሰውን ግፍ በመመልከት እንዲያወግዘው ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም