ቀጥታ፡

ጥቅምት 24 አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ጥቃት የፈጸመበት ዕለት በልዩ ሁኔታ ታስቦ ይውላል

ጥቅምት 21/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ጥቃት የፈፀመበት ጥቅምት 24 ቀን በልዩ ሁኔታ ታስቦ እንደሚውል መንግስት አስታወቀ።

ዕለቱ "አልረሳውም እኔም የኢትዮጵያ ሠራዊት ነኝ" በሚል መሪ ሃሳብ ታስቦ እንደሚውል ተገልጿል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ደሲሳ የጥቅምት 24ቱን ጥቃት መታሰቢያ አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ከ27 ዓመታት ግፍ በኋላ መቀሌ በመመሸግ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ አሻጥሮችን ሲፈጽም ቆይቷል።

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም አገሩን ለውጭ ጠላት አሳልፎ ለመስጠት ከ20 ዓመታት በላይ ለትግራይ ሕዝብ ጠባቂ የነበረውን የሰሜን ዕዝ ሠራዊት በማጥቃትም ክህደት ፈፅሟል።

ሚኒስትር ዴኤታው ዕለቱ ሠራዊቱን ያጠቃበትና የአገሪቷን ከባድ መሳሪያ የዘረፈበት ነበር ብለዋል።

በጥቃቱ ብርቅዬ ጀግኖች በግፍ ተገድለዋል፣ ከባድ መሳሪያዎች ተዘርፈዋል፣ መኮንኖች ታግተዋል፣ ከፍተኛ ጥፋትም ተፈፅሟል።

አሸባሪው ቡድን ጥቃቱን የፈጸመው በሠራዊቱ ውስጥ የኔ የሚላቸውን ሰዎች በመመልመልና በመቶ ሺህዎች የሚቆጠር ጦር በማዘጋጀት ነበር ብለዋል።

ይሁንና ቀሪው ሠራዊት በሁለት ሣምንታት መልሶ ማጥቃት የታገቱትን ማስለቀቁን፣ ወታደራዊ ክንፉ እንዲሰበርና የአሸባሪው ህወሃት አባላትም እንዲያዙ አኩሪ ገድል መፈፀሙን አንስተዋል።

ይህ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የታለመበት ቀን በየዓመቱ ታስቦ ይውላል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ዓላማው  ሕዝባችንን ለቀጣይ ትግል ማነሳሳት ነው ብለዋል።

"አልረሳውም እኔም የኢትዮጵያ ሠራዊት ነኝ" የሚለው መሪ ሃሳብ የተመረጠው ኢትዮጵያን ለማዳን የተወሰዱ እርምጃዎችና የተከፈለውን መስዋዕትነት ታሳቢ በማድረግ መላው ኢትዮጵያዊ በሁሉም መስክ የኢትዮጵያ ሠራዊት መሆን የሚያስፈልግበት ወቅት በመሆኑ ነው ሲሉ አብራርተዋል።

ዕለቱ በመጪው ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡00 ሠዓት የሁሉም የመንግስት ተቋማት ማኅበረሰብ በጋራ በመሆን ለ45 ሰከንድ እጃቸውን ከደረታቸው ላይ በማድረግ ይታሰባል።

በተጨማሪም ዕለቱ በሻማ ማብራት፣ በደም ልገሳና በሌሎች ተግባራት ይዘከራል።

ዕለቱ የኢትዮጵያን ጠላቶች አንገት ለማስደፋት ቀጣይ ትግል የሚያስፈልግበት እንደሆነም አቶ ከበደ አመልክተዋል።

የሽብር ቡድኑ የጥፋት ድርጊት በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ላይ የተፈጸመ ወረራ በመሆኑ ሕዝቡ ለአገሩ ሉዓላዊነት እጅ ለእጅ ተያይዞ መታገል አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም