ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የንግድና የኢንቨስትመንት እድሎች ዙሪያ ውይይት ተደረገ

ጥቅምት 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከ50 በላይ የጀርመን ኩባንያዎች እና ባለድርሻዎች በኢትዮጵያ ያለውን የንግድና የኢንቨስትመንት እድሎች ላይ ውይይት አደረጉ።

ውይይቱ የተደረገው የጀርመን-አፍሪካ የቢዝነስ ማህበር በጀርመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በጋራ ባዘጋጁት የበይነ መረብ መድረክ ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በኢትዮጵያ የህግ እና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በዚህም የጀርመን እና የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ፣በንግድና የኢንቨስትመንት ትስስር ይበልጥ መስፋት አለበት ሲሉ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ የጀርመን ኩባንያዎችን አድንቀው፤ ሌሎችም የነሱን ፈለግ እንደሚከተሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን መንግስት ይበልጥ በሩን መክፈት እና በኢንቨስትመንት ፖሊሲ ላይ በጀርመን ባለሀብቶች የሚነሳው ጉዳይ ትኩረት ይፈልጋል ብለዋል። የጀርመን-አፍሪካ የቢዝነስ ማህበር ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክላውዲያ ቮስ የጀርመን ኩባንያዎቹ በኢትዮጵያ ያሉት የኢንቨስትመንት ዕድሎችን እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።

ከ250 ሺህ በላይ ኩባንያዎች የጀርመን-አፍሪካ የቢዝነስ ማህበር አባል መሆናቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም