ቀጥታ፡

ዩኒቨርሲቲው በ4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ወጪ እያስገነባቸው ያሉ የምርምር ማዕከላት ዘንድሮ ይጠናቀቃሉ

ጥቅምት 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በ4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ወጪ እያስገነባቸው ያሉ ስምንት የምርምር ማዕከላት ዘንድሮ እንደሚጠናቀቁ ገለጸ፡፡

የሳይንስና የቴክኖሎጂ ማዕከል በመሆን እንዲያገለግል ኃላፊነት ተሰጥቶት በ2003 ዓ.ም ወደ ስራ የገባው ዩኒቨርሲቲው የተመሰረተበትን 10ኛ ዓመት ዛሬ ያከበረው ሲሆን በድህረ ምረቃ ዘርፍ አዳዲስ የትምህርት አይነቶች እንደሚጀምር አመልክቷል።  

በሳይንስና ቴክኖሎጂ መስክ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት፣ ቴክኖሎጂን በመቅዳትና የመጠቀም እንዲሁም የፈጠራ ስራን በማከናወን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር ስርዓት ለማሸጋገር የሚደረገውን ጥረት የመደገፍ ኃላፊነት ተሰጥቶታል።

የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ተመስገን ወንድሙ እንዳሉት፤ "የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂና ማኔጅመንት"፣ "የሚነራል ፕሮሰሲንግና ማኔጅመንት"፣ "ቢግ ዳታ አናሊቲክስ"፣ "አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ"፣ "ባዮፕሮሰሲንግ"፣ "ናኖቴክኖሎጂ"፣ "ሚነራል ኤክስፕሎሬሽን" እንዲሁም "የሰስቴነብል ኢነርጂ" እና "ኒውክላር ቴክኖሎጂ" ዘርፎች ማዕከላት እየገነባ ነው።

በ2011 ዓ.ም የተጀመረው የምርምር ማዕከላቱ ግንባታ የውጭ ምንዛሬን ጨምሮ ከግንባታ ግብአቶች እጥረት ጋር በተያያዘ ባጋጠመው ችግር መዘግየት ቢያጋጥመውም ዘንድሮ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል።

የግንባታው የሲቪል ስራ አፈጻጸም ከ75 በመቶ በላይ መድረሱን ገልጸው፤ ግንባታው ሲጠናቀቅ ዩኒቨርሲቲው የያዘውን ራዕይ እንዲያሳካ በማገዝ የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ዘርፍ ለማሻሻል ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተያያዘም ዩኒቨርሲቲው በ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በድህረ-ምረቃ ዘርፍ አዳዲስ የትምህርት አይነቶች ለመጀመር እቅድ መያዙን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል።

"ናኖ ቴክኖሎጂ"፣ "አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ"፣ "ስማርት ማቴሪልያስ" እንዲሁም በሌሎች ከልህቀት ማዕከላቱ ተጓዳኝ ዘርፎች በሁለተኛና በሶስተኛ ዲግሪ ለማስተማር እቅድ መያዙን ገልጸዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ማዕከላት ሆነው እንዲሰሩ በተቋቋሙት የአዲስ አበባ እና የአዳማ  ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች 16 የልህቀት ማዕከላት እየተገነቡ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም በዘርፉ ያለውን አቅም በማጎልበት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለመደገፍ መሆኑን አመልክተዋል።

በሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች እየተደረገ ያለው የልህቀት ማዕከላት ግንባታ ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገቡ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያለውን አቅም ለማሳደግ ሚና እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።

የዩኒቨርሲቲው የምርምር ልህቀት ማዕከላት ግንባታ በቻይና ኮምዩኔኬሽንስ ኮንስትራክሽን ካምፓኒ(ሲሲሲሲ) እና ዮቴክ ኮንስትራክሽን ተቋራጭነት በጋራ እየተከናወነ ይገኛል።

ዩኒቨርሲቲው እስካሁን በቅድመና በድህረ ምርቃ የትምህርት መስኮች ከ9 ሺህ 800 በላይ ተማሪዎችን ያስመረቀ ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት ከሰባት ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም