የአሸባሪው ህወሃትን ከፋፋይ ሴራ በማስወገድ ለአገር አንድነትና ዘላቂ ሰላም መስራት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የአሸባሪው ህወሃትን ከፋፋይ ሴራ በማስወገድ ለአገር አንድነትና ዘላቂ ሰላም መስራት ይገባል
ጋምቤላ፣ ጥቅምት 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት የዘራቸውን ከፋፋይ አስተሳቦች በማስወገድ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና እድገት ማስቀጠል የወጣቱ ትውልድ ቀዳሚ ትኩረት ሊሆን እንደሚገባ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር መኩሪያ ኃይሌ ገለጹ።
የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መስኮች በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 225 ተማሪዎች ዛሬ ሲያስመርቅ በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት ዶክተር መኩሪያ ተመራቂዎች የኢትየጵያን አንድነት የሚሸረሽሩ አስተሳሰቦችን በመታገል ለአገሪቱ ዘላቂ ሰላምና እድገት ጠንክረው እንዲሰሩ አሳስበዋል።
አሸባሪው ህወሃት የፖለቲካ መዋቅሩን በመዘርጋት የኢትዮጵያን ህዝቦች አንድነት በመሸርሸር አገር ለማፈረስ ሲሰራ ቢቆይም ምኞቱ ከንቱ ሆኖ መቅረቱን ገልጸዋል።
ተመራቂዎች ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ አገራቸው የምትፈልግባቸውን አደራ መወጣት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
የዘንድሮው የምረቃ ስነ-ስርዓት አሸባሪው ህወሓት ከውጭ ጠላቶች ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን ለማፍረስ የከፈተውን ጦርነት ለመቀልበስ በወሳኝ ምዕራፍ ወቅት የተካሄደ በመሆኑ የተለየ እንደሚያደርገውም ጠቁመዋል።
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይና የክልሉ ዋና ዐቃቤ ሕግ አቶ አኳይ አቡቲ በበኩላቸው አሸባሪው ህወሃት አገር ለማፍረስ አልሞ የገነባውን አፍራሽ አስተሳሰብ ለማምከን ከተማረው ኃይል ከፍተኛ ስራ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ብቃት ያለው የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፈራትና በክልሉም ሆነ በአገሪቱ ለተጀመረው የለውጥ ጉዞ ስኬት እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።
“በቀጣይም ከመማር ማስተማር ስራው ጎን ለጎን በክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት በምርምር በማገዝ ለማህበረሱ ለውጥ ሊተጋ ይገባል” ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ኡሉጁ ኦኮክ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው የሰለጠነ የሰው ኃይል ከማፍራት ጎን ለጎን በርካታ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን እያካሄደ ይገኛል።
ዩኒቨርሲቲው በባለሙያነት፣ በከፍተኛ አመራርነትና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህዝብ በማገልገል ከፍተኛ አበርክቶ ለነበራቸው አቶ ኡጉታ አዲው የክብር ዶክትሬት ሰጥቷል።