የፈረንሳይ የሐኪሞች ቡድን ለሀሞት ጠጠር ህመም ነፃ የቀዶ ህክምና አገልግሎት ሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
የፈረንሳይ የሐኪሞች ቡድን ለሀሞት ጠጠር ህመም ነፃ የቀዶ ህክምና አገልግሎት ሰጠ
ጅማ፤ ጥቅምት 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) "ቺሩጊ ሶሊዴር" የተሰኘ የፈረንሳይ ግብረ ሰናይ የሐኪሞች ቡድን ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጤና ኢንስቲትዩት የህክምና ማዕከል ጋር በመተባበር በሀሞት ጠጠር ህመም ሲቸገሩ ለነበሩ 24 ሰዎች ነፃ የቀዶ ህክምና አገልግሎት ሰጠ፡፡
የህክምና ማዕከሉ የቀዶ ህክምና ክፍል ኃላፊ ዶክተር ጌርሳም አበራ እንደተናገሩት፤ የሀሞት ጠጠር ቀዶ ህክምና በዓለም ላይ ውድ ከሚባሉ የህክምና አገልግሎቶች ውስጥ ይመደባል።
በማዕከሉ የጠቅላላ ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ሰይፉ አለሙ የሀሞት ጠጠር ቀዶ ህክምናውን ከሰጠው የሐኪሞች ቡድን ልምድ መቅሰማቸውን ገልጸዋል።
“የህክምና አገልግሎቱ ዘመናዊ በመሆኑ ታካሚው በቶሎ አገግሞ ወደ ሥራ እንዲመለስ ከማስቻል ባለፈ የእውቀትና የግብዓት ሽግግር የተደረገበት ነው” ብለዋል።
የሐኪሞቹ ቡድን አባል ዶክተር ዴቪድ ሉክሶ "ወደ ጅማ መጥተን ማገልገልና ልምድ ማካፈል በመቻላችን ደስተኞች ነን” ብለዋል።
በቀጣይም ትብብሩን በማሳደግ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ለረጅም ዓመታት በሀሞት ጠጠር ህመም ሲቸገሩ እንደነበሩ የገለጹት ወይዘሮ አስቴር መቻል፤ "ህክምናውን በመፍራት ቆይቼ ህመሙ ሲጠናብኝ መጥቼ የተሳካ ህክምና አግኝቻለሁ" ብለዋል።
ሌላው ታካሚ አቶ ገመቺስ ጌታቸው ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በሆዳቸው አካባቢ በተከሰተ ህመም ጤንነታቸውን አጥተው ለችግር ተዳርገው እንደቆዩ ተናግረዋል።
ተመርምረው የችግሩ ተጠቂ መሆናቸውን በመረዳት በተመቻቸው ነፃ የህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡