ለመከላከያ ሠራዊት የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን - ኢዜአ አማርኛ
ለመከላከያ ሠራዊት የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን
አርባ ምንጭ፤ ጥቅምት 20/2014 (ኢዜአ) ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች አስታወቁ፡፡
የሚጠበቅባቸውን ሁሉ በማድረግ የሀገር ህልውና ዘመቻውን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ የሚደረገውን ትግል በማገዝ የዜግነት ግዴታቸውን እንደሚወጡ ነዋሪዎቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ለገሠ ሀላቻ እንዳሉት፤ የህወሓት የሽብር ቡድን ኢትዮጵያን የማፍረስ የረጅም ጊዜ እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ነው።
የሽብር ቡድኑ አመራሮች ''ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እንገባለን'' ማለታቸውን ያስታወሱት አቶ ለገሰ፤ የሽብር ቡድኑ ሴራ በገሃድ መውጣቱ የኢትዮጵያ ህዝብ በሀገሩ ጉዳይ አንድ ሆኖ እንዲቆም እንዳስቻለው ተናግረዋል።
አሸባሪው ህወሃት በወረራ በያዛቸው የአማራና አፋር አንዳንድ አካባቢዎች ንጹሃን ዜጎችን በግፍ በመጨፍጨፍና ንብረት በማውደም ታሪክ የማይረሳው አሰቃቂ ተግባር መፈጸሙን አስታውሰዋል።
አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት ከአሸባሪው ህወሓት ጎን በመቆም ቢያሴሩም የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት አንድ በመሆን ጠላትን ማሳፈር እንደቻሉ አመልክተዋል።
ሀሰትን ባህሪው ያደረገው የሽብረ ቡድኑ ህዝቡን ለማወናበድ የሚያሰራጨውን ወሬ ትኩረት እንደማይሰጡት ተናግረዋል።
''ወያኔን የመሰለ ጠላት ይዘን የምንተኛበት ጊዜ አይኖርም'' ያሉት ነዋሪው፤ የሀገር ህልውና ዘመቻው በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የአንድ ወር ደመወዛቸውን መለገሳቸውን ጠቅሰው፤ አሁንም የሚጠበቅባቸሁን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
የህወሓት የሽብር ቡድን ሀገርን ለማፍረስ እየፈጸመ ያለው እኩይ ድርጊት የሚወገዝ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ መስከረም ሀብተገብርኤል ናቸው፡፡
አሸባሪው የህውሓት ቡድን የሃይማኖት ተቋማትን ጨምሮ ሰብአዊና ቁሳዊ ሀብቶችን በማውደም በሀገር ላይ ከፍተኛ ኪሣራ በማድረስ ጥቁር የታሪክ ጠባሳ የጣለ የእናት ጡት ነካሽ መሆኑን ገልጸዋል።
የህልውና ዘመቻውን በድል ለማጠናቀቅ የሚደረገው ትግል በመደገፍ የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ እንደሆኑ ነው ወይዘሮ መስከረም ያስታወቁት።
ወጣት ምስጋና ዱባ በበኩሉ፤ አሸባሪው የህወሓት ቡድን በሰብአዊና ቁሳዊ ሀብት ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት አስነዋሪ መሆኑን ተናግሯል።
ይህንን የሽብር ቡድን ለመደምሰስ ከመከላከያ ሠራዊት ጎን ለመሰለፍ መዘጋጀቱን አስታውቋል።
ሀገርን ከገባችበት ችግር ለማላቀቅና ሰላሟን ለመመለስ መተሳሰብና መደጋገፍ እንደሚያስፈልግ የገለጸችው ደግሞ ወጣት ሊዲያ ጉማራ ናቸው።
የጋሞ ዞን አስተዳደር ሃላፊና የሀብት አሰባሰብ አብይ ኮሚቴ አባል አቶ እሸቱ እልቶ ፤ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የገጠሟትን ፈተናዎች በስልትና በወኔ እየተሻገረች እዚህ መድረሷን ተናግረዋል።
ዛሬም ህዝቡ ከጫፍ ጫፍ የኢትዮጵያን አንድነት አስጠብቆ ለማስቀጠል ቆርጦ የተነሳበት ወቅት ነው ብለዋል፡፡
በዞን ደረጃ ህብረተሰቡ ለህልውና ዘመቻው ከ70 ሚሊዮን በላይ ጥሬ ገንዘብ፣ 320 ሰንጋዎች፣ 189 በጎችና 144 ፍየሎች እንዲሁም በሴቶች የተዘጋጀ ስንቅ ለመከላከያ ሠራዊቱ ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል።
''በሙሉ ልብ ፊታችን ወደ ልማት ለማዞር የህልው ዘመቻውን ማሳጠር ያስፈልጋል'' ያሉት አቶ እሸቱ ፤በ14 ወረዳዎችና ስድስት የከተማ አስተዳደሮች የሚገኘውን ህዝብ በማስተባበር ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።