ቀጥታ፡

አሸባሪው ሕወሓት የከፈተውን ሁሉን አቀፍ ጦርነት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነትና ትብብር መመከት አለበት

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20/2014(ኢዜአ) "የአሸባሪው የሕወሓት ቡድን የከፈተውን ሁሉን አቀፍ ጦርነት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነትና ትብብር መመከት አለበት" ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

"በሁሉም የአገሪቷ አካባቢ መዝመት የሚችል ሁሉ ራሱን ዝግጁ ማድረግ አለበት" ሲልም ጥሪ አቅርቧል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አሻባሪው ህወሃት በአማራና አፋር ክልሎች የከፈተውን ጥቃት አስመልከቶ 'አዳዲስ ክስተቶች ናቸው' ባላቸው ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የአገልግሎቱ ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ፤ አሸባሪው ቡድን መጠነ ሰፊ ጥቃት መሰንዘሩን ተናግረዋል።

''አሸባሪው ቡድን ያለ የሌለ ሀይሉን አሰባስቦ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ፤ ወረባቦና ተሁለደሬ፣ በአፋር ክልል ጭፍራ መጠነ ሰፊ ጥቃት ሰንዝሯል'' ብለዋል።

በነዚሁ አካባቢ የመከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የፀጥታ ሀይሎች እየወሰዱ ባሉት የተቀናጀ እርምጃ'' የሽብሩ ቡድን አባላት ሙትና ቁስለኛ ሆነዋል'' ብለዋል።

ዛሬም በደሴ ዙሪያ 'ቦሩ ሜዳ' በተባለ አካባቢ መከላከያ ሰራዊትና የፀጥታ ሀይሎች ከአሸባሪው ተዋጊዎች ጋር ተጋድሎ እያደረገ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ አየር ሀይልም የሽብር ቡድኑን መጠቀሚያዎች በተሳካ መልኩ ማውደሙን ጠቁመው፤ ለዚህ የሕዝቡ ደጀንነት ተግባር የሚያኮራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ አሻባሪው ህወሃት እያካሄደ ያለው የጦርነት አካሄድ በመደበኛ የውጊያ ስልት ብቻ ሊገታ አይችልም።

ቡድኑ ከ12 ዓመት እስከ 65 ዓመት እድሜ ያላቸው ሰዎችን በጦርነቱ አሳልፎ እኩይ ዓላማውን ለማሳካት እየሰራ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት።

ይህም በመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት በመነሳት ወራሪውን አሻባሪ ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ ዝግጅት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም "በሁሉም የአገሪቷ አካባቢ መዝመት የሚችል ሁሉ ራሱን ዝግጁ ማድረግ አለበት"  ብሏል።

በትናትናው እለት የፌዴራልና የክልል መንግስታት አስፈጻሚዎች አገራዊ ሁኔታውን በማስመልከት ያወጡት መግለጫም ይህንኑ የሚያመላክት መሆኑን ገልጸዋል።

"በየአካባቢው በሚቀርብለት ጥሪ መሰረት አቅም ያለው መዝመት የሚችል ዝግጅት እንዲያደርግ ጥሪ እናስተላልፍለታለን'' ብለዋል።

በየትኛውም አቅጣጫ ያለው ኢትዮጵያዊ "በክልሎች በሚደረግለት ጥሪ መሰረት የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማድረግ መነሳት ይኖርበታል" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በተለይ የውሸት ወሬዎችንና መረጃዎችን የማሰራጨት ስራን እንደ ዋና የውጊያ ስልት እየተጠቀመ መሆኑንም አመልክተዋል።

የሁለተኛው የውጊያ መንገድ የአገሪቷ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዳይናጋ "ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅበትን ይወጣ" ብለዋል።

በተለይም አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን ፈጥኖ ሰብስቦ ለመስኖ ስራ ማዘጋጀት እንዳለበት አሳስበው፤ የመንግስት ሰራተኞችም ያለ እረፍት መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

ነጋዴው፣ አምራች ኢንዱስትሪዎችም የኢኮኖሚ ደጀንነታቸውን በተግባር ለማረጋገጥ ዝግጁ እንዲሆኑ ጠይቀዋል።

አንዳንድ አካላት ጦርነቱን ለመከላከያ ሰራዊትና ጸጥታ ሀይሉ ብቻ የመተው አዝማሚያ መኖሩን አስታውሰው፤ ይህ ትክክል አለመሆኑንና ሁሉም በአንድነት እንዲቆም ነው ያሳሰቡት።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላትም የኢትዮጵያን እውነታ ለማስረዳት ወደ ኋላ ማለት እንደሌላበቸው ነው ሚኒስትሩ ያነሱት።

ቡድኑ ከአንዳንድ አገራትና ግለሰቦች በሳተላይት የተደገፈ መረጃ እያገኘ እንደሆነም ገልጸዋል።

በተለይ ወደ ትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ ቁሳቁስ ጭነው ከገቡ ከአንድ ሺህ አንድ መቶ ተሽከርካሪዎች ውስጥ 860 ያለመመለሳቸው ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም