ኢትዮጵያውያንን በጎሣ እና በመንደር በመከፋፈል ኢትዮጵያ ሕልውናዋን መቼም ልታጣ አትችልም

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያውያንን በጎሣ እና በመንደር በመከፋፈል ኢትዮጵያ ሕልውናዋን መቼም ልታጣ እንደማትችል ብልጽግና ፓርቲ ገለጸ።

ፓርቲው ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ 'ትህነግ አገር ለማፍረስ፤ ኢትዮጵያዊያን አገር ለማዳን' በሚል መሪ ሀሳብ በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ፤ “ኢትዮጵያዊነት የሕብር መገለጫ፣ የዜግነት ክብር እና ኢትዮጵያዊ በመሆን ብቻ የሚገነዘቡት እውነት እንጂ አየር ላይ የተበተነ ጉም አይደለም” ብሏል።

“ለዚህም ነው በሽብርተኛው ቡድን አማካኝነት ለ27 ዓመታት ልዩነትን ብቻ እየጋተ ያሳደጋቸው ወጣቶች ሳይቀሩ ትርክቱን ወዲያ አሽቀንጥረው ጥለው፤ ለአሸባሪው ህወሃት አገራዊ ክህደት ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ሲሉ ቀፎው እንደተነካበት ንብ በአንድ የዘመቱት” ሲል ገልጿል።

“አገር በምንም ልትተካ እንደማትችል የተረዱት እነዚህ ወጣቶች የአገራቸውን መለያ ሰንደቅ ዓላማ ለብሰው ስቅስቅ ብለው ሲያለቅሱ ላስተዋለ ሁሉ የኢትዮጵያ ምንነት እና ኢትዮጵያዊ ማንነት በማያሻማ መልኩ ይገለጹለታል” ብሏል።

አሸባሪው ህወኃት ኢትዮጵያን በቅጥፈት እጆቹ ጠፍጥፎ የጋገራት ህብስት አድርጎ በመቁጠር እሱ ባሻው ሰዓት የሚያቦካትና የሚያፈረካክሳት ጡብ አድርጎ እንደሚቆጥራት የገለጸው ፓርቲው፤ “ኢትዮጵያዊነትን በማንኳሸሽ የሚለወጥ አንዳች ነገር የለም፤ አገር የሁላችንም ምሰሶ ናት፣ አገር ከግለሰቦችና ከቡድኖች በላይ ናት” በማለት አመልክቷል።

እንደ አሸባሪው ቡድን አፈ ቀላጢዎች አባባል ኢትዮጵያ የምትባል አገር ልትኖር አትችልም ነበር ሲል ያስታወሰው ፓርቲው፤ “ኢትዮጵያውያንን በጎሣ እና በመንደር በመከፋፈል ኢትዮጵያ ሕልውናዋን መቼም ልታጣ አትችልም” ብሏል።

“ጥጋብ አላስቀምጥ አላስተኛ ያለው ዘራፊናውና የሽብር ቡድኑ ህወኃት ግን ኢትዮጵያን ለማፍረስ እስከ ሲዖል ለመውረድ መዘጋጀቱን በአደባባይ እየዛተ ይገኛል፤ ዳሩ ከምኞት የዘለለ ባይሆንም” በማለት ገልጿል፡፡

ሽብርተኛው ህወሃት በመላው ሀገሪቱና በሕዝቦች ላይ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ መከራ ሲዘራና ሲያሳጭድ ከመቆየቱም በተጨማሪ ነፃ አወጣዋለሁ የሚለውንም የትግራይ ህዝብ በነፃ አውጪ ስም በርካታ ግፍና መከራ ሲያሸክመው እንደኖረ አስታውሷል።

ህወኃት በሚል የሽፋን ስም የሚንቀሳቀሰው ይህ አሸባሪ ታጣቂ ሃይል የራሱን የፖለቲካ አጀንዳ በማስቀደም አገርን ለከፋ አደጋ ለማጋለጥ ቆርጦ መነሳቱን አሳውቋል፡፡

“አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን አባቶቻችን ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው ከወራሪ ጠላት ያስረከቡንን ውድ አገራችን የወቅቱ የጋራ ጠላታችን የሆነው አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን የማፈራረስ ከንቱ ምኞቱን በሚገባው ቋንቋ አስረድተን እስከወዲያኛው ላይመለስ በአጠረ ጊዜ ልንሸኘው ይገባል” ሲል ፓርቲው በመግለጫው አስገንዝቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም