አሸባሪው ህወሃትን ለመደምሰስ ወጣቱ ከመከላከያ ጎን በመሆን የጀመረውን ትግልማጠናከር አለበት - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሃትን ለመደምሰስ ወጣቱ ከመከላከያ ጎን በመሆን የጀመረውን ትግልማጠናከር አለበት
ባህርዳር ፣ ጥቅምት 20/2014( ኢዜአ) የጠላትን የጥፋት ተልዕኮ ለመቀልበስ ወጣቱ ከመከላከያ ሰራዊት ጋር ጎን በመሆን በሽብር ቡድኑ ላይ የሚወሰደውን እርምጃ ማጠናከር እንዳለበት የአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፍአለ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዘንዘልማ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ተፈናቃዮች 20 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቧል።
በድጋፉ ርክክብ ወቅት ርዕሰ-መስተዳደሩ እንደተናገሩት ሃገርን ለማፍረስ ቆርጦ የተነሳውን አሸባሪ ቡድን ለመደምሰስ ወጣቱ በሁሉም ስፍራ ተዘጋጅቶ ወደ ግንባር በመሰለፍ የሚጠበቅበትን ታሪካዊ ሃላፊነት የመወጣት ተግባር ማጠናከር አለበት።
አሸባሪው ህወሃት አሁን ላይ በደሴ፣ በኮምበልቻ፣ በወረባቦ፣ በተሁለደሬና በደሴ ዙሪያ እያካሔደ ያለውን መጠነ ሰፊ ወረራ የመመከት የተጠናከረ የጀግንነት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
"በዚህ መጠለያ የምትገኙ ወጣቶችም ወደ መጣችሁበት ዋግ ኽምራና ሰሜን ወሎ ዞኖች በመዝመት ህልውናችሁንና ክብራችሁን ለማስጠበቅ መታገል አለባችሁ" ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
"በዛሬው እለት የአዲስ አበባ አስተዳደር ለተፈናቃዮች ያደረገው ድጋፍም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎናችን ለመቆሙ ማረጋገጫ ነው” ብለዋል።
ለተደረገው ድጋፍ በተፈናቃዮች ስም ለከተማ አስተዳደሩ፣ ለህዝቡና ለተሳታፊ አካላት በሙሉ በክልሉ መንግስት ስም ምስጋና አቅርበዋል።
"ወጣቶች በምታካሂዱት ተጋድሎ በህዝባችን ላይ የዘመተውን ጠላት በመደምሰስ የወገኖቻችንን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የክልሉ መንግስት ድጋፍ እንደማይለያችሁ አረጋግጣለሁ" ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው “አሸባሪ ቡድኑ ለዘመናት በኢትዮጵያ ላይ ያደረሰውን ጉዳት፣ ክፋት፣ ሌብነት፣ ዝርፊያና የሰብአዊ መብት ጥሰት ዳግም መፈጸሙ ታሪክ ይቅር የማይለው ድርጊት ነው” ብለዋል።
"አሁን ላይ ሁላችንም በአንድነትና በመተባበር አሸባሪውን ቡድን ታግለን በመደምሰስ ኢትዮጵያን ለማፍረስ መሞከሩ ቀርቶ እንዳያስቡት ለማድረግ በጋራ አርቀን ለመቅበር ዝግጁ ነን" ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩ አሸባሪው ቡድን የአማራ ክልልን ከወረራ ጀምሮ ያደረገው ድጋፍ ለ3ኛ ጊዜ መሆኑን ጠቁመው በአጠቃላይ አንድ ቢሊየን ብር የሚጠጋ የምግብ፣ የቁሳቁስና የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል።
በዛሬው እለት ደግሞ በወረራው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ዜጎች 20 የሚሊየን ብር የሚገመት የምግብ፣ አልባሳት፣ የህጻናት አልሚ ምግብ፣ ዘይትና ሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጉን አስረድተዋል።
"ይህ ወቅት መላ ኢትዮጵያውያን በአንድነት የሚቆሙበት መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል" ያሉት ወይዘሮ አዳነች ድጋፉ “ከድል በኋላ ተፈናቃዮችን ወደ አካባቢያቸው በመመለስ እስከሚቋቋሙ ድረስ ይቀጥላል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት ከቆመ ደግሞ የማናሸንፈው የውስጥም ሆነ የውጭ ሃይል የለም ሲሉም ተናግረዋል።
ህወሃት ጦርነት ከከፈተ ወዲህ ብቻ በክልሉ ከ900 ሺህ በላይ ንጹሃን ዜጎች ተፈናቅለው እርዳታና ድጋፍ ጠባቂ መሆናቸውን ከክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።