የፀጥታ ሀይሉ በሚፈጽመው የተቀናጀ ማጥቃት አሸባሪው ቡድን ላይ ድል እየተቀዳጀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፀጥታ ሀይሉ በሚፈጽመው የተቀናጀ ማጥቃት አሸባሪው ቡድን ላይ ድል እየተቀዳጀ ነው
ጥቅምት 20/2014 (ኢዜአ)የጸጥታ ሀይሉ በሚፈጸመው የተቀናጀ ማጥቃት የአሸባሪውን ህወሃት ቡድን እየደመሰሰና ድል እየተቀዳጀ መሆኑን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ተሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የአገልግሎቱ ሚኒስትር ዶክተር ለገሠ ቱሉ እንደገለጹት፤ የፀጥታ ሀይሉ በሚፈጸመው የተቀናጀ ማጥቃት ድል እየተቀዳጀ ነው።
የአሸባሪው ህወሃት ቡድን ባለፋት ጥቂት ቀናት ያለውን ሀይል አሰባስቦ በወረባቦ፤በተሁለደሬ እና በጭፍራ ጥቃት መክፈቱን አስታውሰዋል።
የፀጥታ ሀይሎች በወሰዱት የአጸፋ እርምጃ "የአሸባሪው ህወሃት አባላት ሙትና ቁስለኛ ሆነዋል" ብለዋል።
አየር ሀይሉ እየወሰደ ባለው እርምጃም በተሳካ መልኩ የአሸባሪው ህወሃት መጠቀሚያዎችን ማውደም መቻሉንም አብራርተዋል።
አሁንም ቡድኑ እኩይ ድርጊቱን የቀጠለ መሆኑን አመልክተው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ከምን ጊዜውም በላይ በአንድነት መነሳት እንዳለበት አብራርተዋል።
"በሁሉም የአገሪቷ አካባቢ መዝመት የሚችል ሁሉ ራሱን ዝግጁ ማድረግ አለበት" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ህዝቡ እንደ ሰራዊት በሁሉም መስክ ለአገሩ አስተዋጽኦ ለማድረግ ራሱን ማዘጋጀት እንዳለበት ተናግረዋል።
ከዚህም ባለፈ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የአገሪቷ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲቀላጠፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።